
ባሕር ዳር: ኅዳር 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያውን ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ የሴክተር ጉባኤ በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ.ር)፣ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ እና ሌሎችም የፌዴራል እና የክልሉ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ በአማራ ክልል ሰላም እየሰፈነ ሕዝቡም በሰላም ሥራውን እያከናወነ ነው ብለዋል።
የክልሉ መንግሥትም ተገቢውን የልማት ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። መንግሥት ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለቱሪዝም፣ ለማዕድን፣ ለከተማ ልማት እና ለሌሎችም ሴክተሮች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
እንደ ሀገር የብልጽግና ጉዞ መዳረሻ ይኾናሉ ተብለው የታቀዱት የግብርና ግብዓቶች ብዙዎቹ በአማራ ክልል እንደሚገኙ አንስተዋል።
በሴክተሮች የታቀዱት የልማት ዕቅዶች ለስኬት እንዲበቁ የትራንስፖርት እና የሎጅስቲክስ ዘርፉ ወሳኝ ነው ብለዋል። እንደ ሀገር ለትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ዘርፍ ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠው ሁሉ በአማራ ክልልም በልዩ ትኩረት እየተሠራበት እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ዘርፉ ብዙ ተገልጋይ ያለበት በመኾኑ ውስንነቶቹን መቅረፍ በርካታ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ይፈታል ብለዋል። ዘርፉን በዘመናዊ መንገድ ለመምራት ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት።
የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ለክልሉ በርካታ ድጋፎች ማድረጉን አንስተው ጉባኤውን በባሕር ዳር በማድረጉ የሚመሠገን ነው ብለዋል። ክልሉን በርቀት ኾነው ልማት እና ሰላም እንደሌለ አድርገው ለሚያዩት ሁሉ ዕውነታውን ያሳየ መኾኑንም አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
