
ጎንደር: ኅዳር 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዳሽን ቢራ ፋብሪካ በጎንደር ከተማ ለሚገኘው አዘዞ ጤና ጣቢያ ግምቱ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ዘመናዊ የሕክምና መሳሪያ ነው ድጋፍ ያደረገው።
የዳሽን ቢራ ፋብሪካ የማኅበራዊ ዘርፍ ኀላፊ እንዳልካቸው አበበ ፋብሪካው የአዘዞ ጤና ጣቢያን የሕክምና መሳሪያ እጥረት በመረዳት በግማሽ ሚሊዮን ብር የአልትራሳውንድ ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።
ድጋፉ ባለሙያዎች በመሳሪያ የተደገፈ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት የተሻለ ሥራ እንዲያከናውኑ ዕድል እንደሚፈጥርም አንስተዋል።
ፋብሪካው በተያዘው ዓመት ለ30 ሺህ ተማሪዎች የደብተር ድጋፍ ማድረጉንም ኀላፊው አስታውሰዋል።
በጤና ጣቢያው ከዚህ በፊት የአልትራሳውንድ ማሽን ባለመኖሩ ወላድ እናቶች አገልግሎት ለማግኘት ወደ ሌላ ቦታ ይሄዱ እንደነበር ያስታወሱት ድጋፉን የተረከቡት የአዘዞ ጤና ጣቢያ ኀላፊ ዩሐንስ በሪሁን ናቸው።
ድጋፍ መደረጉ ወላድ እናቶች በተገቢው መንገድ አገልግሎት እንዲያገኙ ሌሎች ሕክምናው የሚያስፈልጋቸው ሕሙማንም የአልትራሳውንድ ምርመራን በማግኘት የሚያጋጥማቸውን የጤና ችግር የሚቀርፍ መኾኑንም ተናግረዋል።
ሌሎች ተቋማትም ለጤና ጣቢያዎች ድጋፍ በማድረግ ማኅበረሰቡ የተሟላ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ የበኩላቸውን እንዲወጡም የጤና ጣቢያው ኀላፊ ጥሪ አቅርበዋል
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ ዳሽን ቢራ ፋብሪካ በከተማ አሥተዳደሩ ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር፤ ለከተማዋ የኮሪደር ልማት 10 ሚሊዮን ብር በመለገስ እና በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን በጎ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ፋብሪካው በአዘዞ ጠዳ ክፍለ ከተማ ለሸድ ግንባታ ድጋፍ ማድረጉን ያስታወሱት ምክትል ከንቲባዋ አሁን ላይ ለአዘዞ ጠዳ ጤና ጣቢያ ላበረከተው የአልትራ ሳውንድ ድጋፍም ምሥጋና አቅርበዋል።
የማኅበረሰቡን ጤና ለመጠበቅ እና አምራች ትውልድ ለመፍጠር ፋብሪካው ለጤና ጣቢያው ያደረገው ድጋፍ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለውም ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
