
አዲስ አበባ፡ ኅዳር 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ.ር) በሀገር አቀፍ ደረጃ በሆሳዕና ከተማ የሚከበረውን 20ኛው የብሔር፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል አከባበር ዝግጅትን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በፌደሬሽን ምክር ቤት አዘጋጅነትና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት የሚካሄደውን 20ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በስኬት እንዲከበር በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
የበዓሉ መከበር ሀገርን የሚያሻግሩ የጋራ ገዢ ትርክቶችን በመገንባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት አቅም እንዲሆኑ የማስቻል ትልቅ ፍይዳ አለው ብለዋል። የሕዝብ አንድነት አጠናክሮ ለማስቀጠል፣ የልማት እንቅስቃሴዎችን በጥራትና በብዛት ለመሥራት አቅም ለመፍጠር እና ያሉትን ጸጋዎች ተጠቅሞ በአግባቡ ለማደግም እድል የሚፈጥር እንደኾነም አንስተዋል።
በዓሉን ተከትሎ በርካታ እንግዶች ወደከተማዋ እንደሚገቡም ጠቅሰዋል። ለተሳታፊዎች በቂ ማረፊያዎች ተዘጋጅተዋል፤ በዓሉ የሚከበርበትን ስታዲየም እድሳት የማጠናቀቅ እና ሌሎች በዓሉን በደማቅ ሁኔታ ለማክበር የሚያስችሉ የሰላምና ጸጥታ ሥራዎችም ተሠርተዋል ብለዋል።
የክልሉን ኢንቨስትመንት የሚያነቃቁ የልማት ሥራዎች፣ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማልማት፣ ለማዕድን ጥናት እና የግብርና ሥራዎችን በትኩረት ለመሥራት የሚያስችል ትልቅ መነቃቃት መፈጠሩንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን የክልሉ አሥተዳደራዊና ፓለቲካዊ ማዕከል እና የብዝኀነት ማዕከል ወደኾነችው ሆሳዕና ከተማ መጥተው በዓሉን በአብሮነት እንዲያከብሩም ጥሪ አቅርበዋል። እንግዶቻችንን ተቀብለን ለማስተናገድ ተዘጋጅተናል ነው ያሉት።
የአካባቢው ማኅበረሰብም በተለመደው እሴቱ ተሳታፊዎችን እንዲቀበልና እንዲያስተናግድ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
