የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ብዝኅነትን በአንድነት፣ አንድነትን በብዝኅነት የምናሳይበት ልዩ ቀን ነው።

2
ሰቆጣ: ኅዳር 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን “ዴሞክራሲያዊ መግባባት፣ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልዕክት በሰቆጣ ከተማ ተከብሯል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንታይቱ ካሴ የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን መከበር ለዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ራሱን በራሱ እንዲያሥተዳድር፣ ባሕሉን እንዲጠብቅ እና ቋንቋውን እንዲያሳድግ ዕድል የፈጠረ በዓል ነው ብለዋል።
ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ ማሰጠት ይገባል ነው ያሉት። ለዚህም መላው ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ለማጠናከር እና ውስጣዊ ሰላምን ለማረጋገጥ ቃል በመግባት በዓሉን ማክበር ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።
በበዓሉ ላይ የብሔር ብሔረሰቦችን ባሕላዊ ውዝዋዜ ያሳዩት የሻደይ ባሕል ቡድን አባል ወንድሙ ሞገስ በዓሉ ሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር የሚያሳዩበት እና አንድነታቸውን ለዓለም መድረክ የሚያሳዩበት መኾኑን ገልጿል።
እኩልነትን በአደባባይ ለማሳየት የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ትልቁ መድረክ ነው ያሉት ደግሞ የበዓሉ ተሳታፊ ወይዘሮ ኪሮሱ ፀሐዩ ናቸው።
ይህንን ኅብረ ብሔራዊ በዓል ጠብቆ ማስቀጠል ያስፈልጋል ያሉት ወይዘሮ ኪሮሱ ለኢትዮጵያውያን የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ብዝኅነትን በአንድነት፣ አንድነትን በብዝኅነት የምናሳይበት ልዩ ቀን ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ኢትዮጵያ በርካታ ማዕድን ያላት ግን በሚገባት ልክ ሳትጠቀም የቆየች ሀገር ናት” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ