ምርት እንዳይባክን በጥንቃቄ መሠብሠብ ያስፈልጋል።

7
ደብረማርቆስ: ኅዳር 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ብክነትን በመቀነስ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለገበያ ለማቅረብ አርሶ አደሮች የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ እንዲሠበሥቡ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ አሳስቧል፡፡
እስካሁን በዞኑ 23 በመቶ የሚኾነውን የሰብል ምርት መሠብሠብ መቻሉን መምሪያው አስታውቋል፡፡
በምሥራቅ ጎጃም ዞን በ2017/18 የምርት ዘመን ከ641 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ማሳ በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል። ከ25 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሠብሠብ ታቅዶ እየተሠራ ነው።
በዞኑ የደረሱ ሰብሎችን የመሠብሠብ ሥራውም በስፋት ተጀምሯል።
በምርት ዘመኑ ከታቀደው 23 በመቶ የሚኾነውን መሠብሠብ መቻሉን የገለጹት የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አበበ መኮነን ናቸው።
ምርትን ከብክነት በመከላከል ጥራት ያለው ምርት ለመሠብሠብ የሚያስችሉ የተለያዩ የሰብል ማጨጃ እና መውቂያ ማሽኖችን በስፋት በማሰማራት ምርት በፍጥነት እንዲሠበሠብ እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡
በምርት ዘመኑ ለማምረት የታሰበውን የሰብል ምርት ለማግኘት የሚያስችል የሰብል ቁመና መኖሩንም አንስተዋል።
አርሶ አደሮች ያመረቱትን ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይባክን ቀድመው የሚደርሱ ሰብሎችን የተለያዩ አማራጮችን ተጠቅመው በመሠብሠብ ከማሳ እስከ ጎተራ ምርት እንዳይባክን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
አርሶ አደሮች ከሰብል ማሠባሠብ ጎን ለጎን የበጋ መስኖ ልማት እና የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ ዝግጅትን በስፋት እንዲያከናውኑም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ሰላም፣ አንድነት እና ፍቅር የሚሰበክበት የኢትዮጵያውያን ቀን ነው።
Next article“ኢትዮጵያ በርካታ ማዕድን ያላት ግን በሚገባት ልክ ሳትጠቀም የቆየች ሀገር ናት” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ