
ደብረማርቆስ: ኅዳር 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 20ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን “ዲሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልዕክት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር እና የምሥራቅ ጎጃም ዞን የመንግሥት ሠራተኞች በተገኙበት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ መርከብ የሻነው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል ላለፉት ዓመታት መከበሩ የተለያዩ ብሔረሰቦች ማንነት በሚገባ እንዲታይ እና እንዲታወቅ በማድረግ የላቀ አስተዋጽኦ አበርክቷል ነው ያሉት፡፡
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የከንቲባ ተወካይ እና የሥራ እና ክህሎት መምሪያ ኀላፊ መኮንን ሙሉዓዳም ብዝኅነት የሀገሪቱ ኅብረ ብሔራዊነት መሠረት መኾኑን ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት የኅብረ ብሔራዊነት ግንባታን የሚፈታተኑ ችግሮች ቢያጋጥሙም መንግሥት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሲቪል ሰርቪስ የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ሸጋው ሙሉ የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል ኢትዮጵያውያን ከመገፋፋት በመውጣት በመተሳሰብ እና በመደጋገፍ መኖር እንደሚገባቸው ማሳያ መኾኑን ገልጸዋል።
የበዓሉ ተሳታፊዎችም የመንግሥት ሠራተኞች በዓሉን ሲያከብሩ ዕውነተኛ እህት፣ ወንድማማችነትን እና አብሮነትን በማጠናከር ለጋራ ተጠቃሚነት በመትጋት እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
በዓሉ በዚህ ወቅት መከበሩ እንደ ሀገር የሚታዩ ግጭቶች እና አለመግባባቶችን ተቀራርቦ በውይይት ለመፍታት ሁሉም የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ያግዛል ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
