የአፍሪካ እና ባንግላዴሽ ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንዲኖር ያስችላል።

2
አዲስ አበባ: ኅዳር 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአፍሪካ ሀገራት እና በባንግላዲሽ መካከል የሁለትዮሽ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትብብርን ለማጠናከር ያለመ የመጀመሪያው የአፍሪካ ባንግላዲሽ የንግድ ትርኢት እና የቢዝነስ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የጉባኤው ዋና ዓላማ የባንግላዲሽ ላኪዎች፣ ሥራ ፈጣሪዎች እና ባለሃብቶችን ከአፍሪካ የዘርፉ ተዋንያን እና የኢንዱስትሪ ባለድርሻ አካላት ጋር ማገናኘት ነው።
በኢትዮጵያ የባንግላዴሽ አምባሳደር ሲትዋት ናኢም ኢትዮጵያ እና ባንግላዲሽ በዘላቂ ልማት ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል መልካም ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው ብለዋል።
ሁለቱን ሀገራት በንግድ እና ኢንቨስትመንት በጋራ ለማስተሳሰር፣ ተጠቃሚ ለማድረግ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ዝግጁ እንደኾኑ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምሥራቅ፣ የእስያ እና የፓስፊክ ሀገራት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ደዋኖ ከድር የኢትዮጵያ እና ባንግላዴሽ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እ.ኤ.አ 1975 የጀመረ እና 50 ዓመታትን ያስቆጠረ መኾኑን ተናግረዋል።
ከባንግላዴሽ በዋናነት የፋርማሱቲካል ምርቶች እንደሚገቡ እና ባንግላዴሽ ደግሞ የቡና ምርትን በቀዳሚነት ከኢትዮጵያ ትወስዳለች ነው ያሉት።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ድኤታ ይድነቃቸው ወርቁ የዓለም ንግድ እንቅስቃሴ በፍጥነት እየተቀየረ ነው ብለዋል። በአፍሪካ እና ባንግላዴሽ መካከል ግንኙነት መፈጠሩ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ለዚህ ያግዛል ያሉት ሚኒስትር ድኤታው ባንግላዲሽ በኢትዮጵያ ንግድ እና ኢንቨስትመንት እንድትሳተፍ ዕድሎችን ለመፍጠር እና የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሠራል ብለዋል።
ስድስት የባንግላዴሽ የንግድ ኩባንያዎች አሁን ላይ በኢትዮጵያ እየሠሩ እንደሚገኙ ተገልጿል።
አልባሳት፣ የቆዳ ውጤቶች፣ ፋርማሲዩቲካል፣ ግብርና፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና ምህንድስና በሁለቱ ወገን በጋራ ይሠራባቸዋል ተብለው የሚጠበቁ ዘርፎች መኾናቸው በጉባኤው ተጠቁሟል።
ዘጋቢ ፦መሠረት መቅጫ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበቅንጅት በመሥራት የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ደህንነት መጠበቅ ይገባል።
Next articleየብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ለኅብረ ብሔራዊነት ግንባታ አስፈላጊ ነው።