
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 09/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸው ወደ ለይቶ ማከሚያ ያልገቡትን አሽከርካሪዎች እና ንክኪ ያላቸውን ሰዎች የማፈላለጉ ሥራ መቀጠሉን የሰሜን ሸዋ ዞን ጤና መምሪያ አስታውቋል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን 22 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡን የዞኑ ጤና መምሪያ ትናንት መግለጹ ይታወሳል፡፡ በ79 ሰዎች ላይ ምርመራ ተደርጎ ነበር 22 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው፡፡
ከ79 ተመርማሪዎች 36 አሽርካሪዎች እንደነበሩና ከእነዚህ መካከል 16 የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸውም ዘግበን ነበር፡፡
ቫይረሱ ከተገኘባቸው 22 ሰዎች መካከል 16ቱ አሽከርካሪዎች እየተፈለጉ እንደሚገኙ የዞኑ ጤና መምሪያ ለአብመድ ገልጾ ነበር፡፡ አሁን በደረሰን መረጃ መሠረት ደግሞ ስድስት አሽከርካሪዎች ተገኝተዋል፤ ወደ ለይቶ ማከሚያ ማዕከልም ተወስደዋል፡፡ ሌሎችን አሽከርካሪዎች እና ንክኪ ያላቸውን ሰዎች የማፈላለጉ ሥራ መቀጠሉንም ጤና መምሪያው አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል ትናንት ሰኔ 8/2012 ዓ.ም ይፋ የተደረገ መረጃ እንደሚያሳየው ከ624 የላቦራቶሪ ምርመራ በ33 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቷል፡፡
በክልሉ እስከ ትናንት ሰኔ 8/2012 ዓ.ም ድረስ ለ5 ሺህ 590 ሰዎች የናሙና ምርመራ ተደርጎ በ231 ሰዎች ቫይረሱ መገኘቱን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ በክልሉ አጠቃላይ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥርም 44 መድረሱን መዘገባችን ይታወቃል፡፡
ዘጋቢ፡- ኤልያስ ፈጠነ -ከደብረ ብርሃን
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡