
ደባርቅ: ኅዳር 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ደኅንነት ለማስጠበቅ በሚቻልባቸው የሕግ ማዕቀፎች ዙሪያ የሰሜን ጎንደር ዞን የዳኝነትና የፍትሕ አካላት እና የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት የጋራ ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ ተቋማቱ በቀጣይ በተጠናከረ መንገድ አብረው መሥራት የሚያስችላቸውን የጋራ ሰነድ አጽድቀዋል።
የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኀላፊ ላቀው መልካሙ የጋራ ስምምነቱ በፓርኩ ዙሪያ የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል እና ተፈጽመው ሲገኙም አፋጣኝ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
በቀጣይም የሕግ ጉዳዮችን በሚመለከት የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን ለማመቻቸት እና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ለመሥራት እንደሚያስችልም ነው የተናገሩት።
የሰሜን ጎንደር ዞን ተወካይ አሥተዳዳሪ እና የሲቪል ሰርቪስ መምሪያ ኀላፊ ያሬድ አበበ “ቱሪዝም ለዞኑ ትልቅ የልማት አቅም ነው” ብለዋል። ስለኾነም ይሄን የልማት አቅም ለማስቀጠል የቱሪዝም መስህብ የኾነውን የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን መንከባከብ እና መጠበቅ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የጥበቃ ሥራውን ለማጠናከር እና ለማስቀጠል በዞኑ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር ጥምረት እና በፓርኩ ጽሕፈት ቤት የጸደቀው ሰነድ ወሳኝ መኾኑን ነው የተናገሩት።
የሰሜን ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና የዞኑ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር ጥምረት ሰብሳቢ ግዛቸው ሙጬ ከዚህ በፊት ከፓርኩ ጋር በትብብር ሢሠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል። በቀጣይም አብሮነታቸውን ለማጠናከር የጋራ ሰነድ አዘጋጅተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ነው የተናገሩት።
ይሄም ሰነድ በፓርኩ ዙሪያ የሚካሄዱ ሕገ ወጥ አደን እና መሰል ጉዳዮችን ለመከላከል እና ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ መግባባት የተደረሰበት መኾኑን አብራርተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
