ስለሪህ በሽታ ምን እንወቅ?

1

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሪህ በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት የሚችል የህመም ዓይነት ነው።
የሚከሰተው ዩሪክ አሲድ የተባለው ኬሚካል በአጥንት መገጣጠሚያዎች ውስጥ በሚከማችበት ወቅት እንደኾነ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሪህ ህመም ተጠቂ ባለታሪክ ህመሙ እንዳለባቸው ካወቁ ስምንት ዓመት መቆጠሩን ገልጸውልናል። ሲጀምራቸውም የእግራቸው አውራ እጣት ላይ እንደነበር አስታውሰዋል።

በጊዜ ሂደት ደግሞ ወደ ሌሎች መገጣጠሚያ አካባቢዎች ከፍ እያለ መሄዱንም አጫውተውናል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ለመንቀሳቀስ የሚያስቸግር ስሜት እንዳለው ነው የተናገሩት ። በዚህ ጊዜ ለሥራ አስቸጋሪ እንደሚኾንባቸው ተናግረዋል።

“ግንዛቤው ስለሌለኝ ሕክምና ከመሄዴ በፊት የወለቀ ነገር ያለኝ መስሎኝ ወደ ወጌሻ ሄጀ ነበርም ነው ያሉን። በዚህም ህመሙ ከመባባስ ውጭ ለውጥ አለማግኘታቸውን ጠቅሰዋል።

ወደ ሕክምና ተቋም ሄደው ምርመራ ሲያደርጉም የሪህ ህመም እንዳለባቸው ማረጋገጣቸውን ነው ያስታወሱልን። አሁን ላይ የሕክምና ክትትል እያደረጉ እንደኾነም ገልጸውልናል።

ማኅበረሰቡ ተገቢ የሕክምና ምርመራ በማድረግ ከሚፈጠሩ ህመሞች ራሱን እንዲጠብቅም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በፈለገ ሕይዎት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ሐኪም ዶክተር እስከዳር ስለሺ ሪህ ረጅም ጊዜ የሚቆይ በዋናነትም መገጣጠሚያዎችን የሚያጠቃ በሽታ መኾኑን ነግረውናል።

ሳንባን፣ ልብን እና ነርቮችን ሊያጠቃ እንደሚችልም ጠቅሰዋል። ዝቅተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ተብለው የሚገለጹ ሦሥት ደረጃዎች እንዳሉትም አንስተዋል።

የመጀመሪያ ደረጃ የሚባለው የሪህ ህመም መገጣጠሚያ አካባቢ ህመም እና እብጠት የመኖር ምልክት እንዳለው ነው የገለጹት።

ታማሚዎች ሕክምና ካልጀመሩ ደግሞ ሁለተኛ እና ሦሥተኛ ደረጃ የሚባሉ የመገጣጠሚያ መሸርሸር፣ የአጥንት መጣመም እና የእንቅስቃሴ መወሰን ይኖራል ነው ያሉት። ብዙ ሰዎች ህመም ሲሰማቸው ቶሎ ወደ ጤና ተቋም ያለመሄድ ችግር እንደሚስተዋልም ጠቅሰዋል።

የሪህ በሽታ መንስኤ ይሄ ነው ብሎ ማስቀመጥ እንደሚያስቸግር የተናገሩት ዶክተር እስከዳር አጋላጭ ኹኔታዎች ግን አሉ ነው ያሉት። ማጨስ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ ጾታ፣ የዕድሜ መጨመር እና አንዳንዴ ደግሞ በዘር ካለም ተጋላጭ እንደሚያደርግ አንስተዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ያጠናውን ጥናት ጠቅሰውም ከጾታ አንጻር ሴቶች የበለጠ ተጋላጭነታቸው ከፍ እንደሚል ነው የተናገሩት። ብዙ ጊዜም የደም እና የራጅ ምርመራዎች እንደሚደረጉ ጠቅሰዋል።

በሽታው አንዴ ከተረጋገጠ በኋለ ክትትሉም ለረጅም ጊዜ የሚደረግ እንደኾነ ጠቅሰዋል።

ለሪህ በሽታ የሚሰጡ መድሃኒቶች ህመሙን ባለበት እንዲቆይ የሚያደርጉ እንጅ ሙሉ በሙሉ የሚያጠፋ አለመኾናቸውን ነው የገለጹት። የዕለት ከዕለት ሥራ እንዳይደናቀፍም መድሃኒቶች እና የሕክምና ባለሙያዎች ምክር ያግዛሉ ብለዋል።

በሕክምና ተረጋግጦ የሪህ በሽታ የተገኘበት ሰው ወዲያውኑ መድሃኒት መጀመር እና በተገቢ ኹኔታ መውሰድ እንደሚገባም መክረዋል። የተመጣጠነ እና አትክልት የበዛበት ምግብ መመገብ፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ስጋ እና ሌሎች ፕሮቲን የበዛባቸውን ምግቦች አለመመገብ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

ፊዚዮቴራፒ ማድረግ እና ፈሳሽ ነገር በደንብ እንዲወስዱም ይመከራል ብለዋል። ከጊዜ ጋር የሚሄዱ በሽታዎችን በጊዜው በሕክምና ለመመለስ ሰዎች ቅድመ የጤና ምርመራ እንዲያደርጉም መክረዋል።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበር ሀገራዊ እሴቶች እንዲጠበቁ ያስችላል።
Next articleበቅንጅት በመሥራት የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ደህንነት መጠበቅ ይገባል።