
አዲስ አበባ: ኅዳር 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልዕክት በሆሳዕና ከተማ ይከበራል።
ኢትዮጵያ የብዝኀ ሃይማኖቶች፣ ማንነቶች፣ ቋንቋዎች እና ባሕሎች መገኛ ኅብረብሔራዊት ሀገር ናት። ባለፉት 19 ዓመታት በኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት ሲከበር የቆየው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ሕዝቦች ያላቸውን የተለያዩ እምቅ እሴቶችን በማስተዋቅ እና ጎልተው እንዲወጡ በማድረግ ረገድ የጎላ ሚና እንዳለው በፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግሥታት ግንኙነት፣ የዴሞክራሲ አንድነት እና የሕገመንግሥት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ ባንቺይርጋ መለሰ ተናግረዋል።
የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ሲከበር በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ መስኮች የተገኙ ስኬቶችን በማስቀጠል ለቀጣይ ዕድገት እና ብልጽግና መትጋት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ዜጎች በሕገመንግሥቱ እና በፌዴራል ሥርዓቱ ዙሪያ ተቀራራቢ ዕውቀት እንዲኖራቸው እንደሚያደርግም አብራርተዋል። በፌዴራል ሥርዓቱም ላይ ግንዛቤ በመፍጠር ዕድገት እና አብሮነትን ለማስተሳሰር የጎላ ሚና እንዳለውም አመላክተዋል።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ከሕዳር 1 ጀምሮ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች በልዩ ልዩ ሁኔታዎች እንደሚከበር ወይዘሮ ባንቺይርጋ መለሰ አስረድተዋል።
ከሕዳር 25/2018 ዓ.ም ጀምሮም የአምስት ቀናት ደማቅ ክንውኖችን አካትቶ “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልዕክት በሆሳዕና ከተማ ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች በተውጣጡ የባሕል አምባሳደሮች እና ተወካዮች በተለያዩ የማጠቃለያ መርሐ ግብሮች ሕዳር 29 ቀን በድምቀት እንደሚከበር ተነግሯል።
ኢትዮጵያ በሁሉም አውዶች አሸናፊ እንድትኾን ለማስቻል ከመገፋፋት ይልቅ መደጋገፍ፣ ከጥላቻ ይልቅ መተሳሰብ፣ ከሚለያዩ ትርክቶች ይልቅ የሚያሠባሠቡ ዕውነታዎች ላይ ማተኮር ይገባል ብለዋል። ለጋራ ህልም እና ርዕይም ሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራውን ማሳረፍ እንደሚገባው በመግለጫው ተጠቁሟል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
