
ባሕር ዳር: ኅዳር 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዓባይ ጋርመንት ፋብሪካ በጎንደር ከተማ የሚገኝ ግዙፍ ፋብሪካ ነው። በ2009 ዓ.ም በዓባይ ኢንዱስሪ ልማት አክሲዮን ማኅበር አማካኝነት ግንባታው ተጀምሮ በ2012 ዓ.ም ወደ ምርት የገባ ፋብሪካ ነው።
በዕለቱ ለፋብሪካው 500 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ካፒታል ተይዞለት ነበር ወደ ሥራ የተገባው።
ፋብሪካው 80 በመቶ ለውጭ ገበያ እንዲሁም 20 በመቶ ደግሞ ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚቀርቡ አልባሳትን በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለማስገኘት ታሳቢ ተደርጎ የተቋቋመ ነው። ለሥራ ዕድል ፈጠራም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተስፋ የተጣለበት ፋብሪካም ነው።
የፋብሪካው ሠራተኛ ወጣት ፈንታሁን መርሻ በቴክስታይል ኢንጅነሪንግ ከተመረቀ በኋላ ለሥራ ፍለጋ ከአካባቢው ርቆ በአዲስ አበባ እና በሀዋሳ መቆየቱን ከአሚኮ ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጾልናል።
ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በፋብሪካው የሥራ ዕድል ተፈጥሮለት እየሠራ እንደሚገኝም ነው የነገረን። ይህም በተመረቀበት የሙያ መስክ ከቤተሰብ ሳይርቅ ሥራ ማግኘት እንዳስቻለው ገልጿል። በአሁኑ ወቅትም ሕይዎቱን በተሻለ መንገድ መምራት እንዳስቻለውም ነግሮናል።
ለሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎችም የሥራ ዕድል እየፈጠረ የበርካታ ዜጎችን ሕይዎት እየቀየረ እንደኾነም አስተያየቱን ለአሚኮ ሰጥቷል።
ሌላው አስተያየቱን የሰጠው ወጣት እሸቱ ሙጨ በፋብሪካው ከ2 ዓመታት በላይ ሲሠራ መቆየቱን ነግሮናል። በፋብሪካው ውስጥ ሢሠራ ባገኘው እውቀት እና ልምድ ተጠቅሞ አሁን ላይ የራሱን የግል ድርጅት መሥርቶ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግሯል።
ፋብሪካው ሠራተኛ ቀጥሮ ከማሠራት በተጨማሪ የእውቀት ሽግግር እንዲኖር አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጿል። ሠራተኞች የራሳቸውን ድርጅት አቋቁመው ለመሥራት ዕድል እየፈጠረ ስለመኾኑም አብራርቷል።
የዓባይ ጋርመንት ፋብሪካ ሥራ አሥኪያጅ ሰለሞን ጋሻው ፋብሪካው ሥራ የጀመረው 130 ሠራተኞችን በመያዝ እንደነበር አስታውሰዋል።ሥራ በጀመረበት ዓመትም 80 ሺህ የሚኾኑ አልባሳትን በማምረት ለገበያ አቅርቦ እንደነበር ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት ለ800 ቋሚ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም አስታውቀዋል።
ፋብሪካው ሥራ ሲጀምር ደረጃቸውን የጠበቁ ማሽኖችን በመጠቀም ለውጭ ገበያ የማቅረብ ዕቅድ እንደነበረው ነው የተናገሩት።
በታቀደው መሠረት ለመፈጸም ግን በኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ በሰሜኑ ጦርነት፣ የአፍሪካ የዕድገት እና የገበያ ዕድል (AGOA)መቅረት ተጽዕኖ እና በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ምርቱን ለውጭ ገበያ ተደራሽ ለማድረግ አለመቻሉን አመላክተዋል። ምርቱን ከውጭ ገዥዎች ጋር ለማገናኘት መቸገራቸውንም አንስተዋል።
ፋብሪካው የገበያ ችግር እንጂ የማምረት ችግር እንደሌለበት ነው የገለጹት። ችግሩን መነሻ በማድረግም የገበያ ስትራቴጅ ለውጥ በማድረግ ወደ ሀገር ውስጥ ገበያ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ስለመኾኑም አመላክተዋል።
ሥራ አሥኪያጁ እንደገለጹት በ2017 በጀት ዓመት 426 ሺህ ተኪ የአልባሳት ምርቶችን በማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያ አቅርቧል። ከዚህም የ125 ሚሊዮን ብር ሽያጭ ተፈጽሟል ነው ያሉት። 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ማስቀረቱንም ጠቁመዋል።
በዚህ ዓመት እስከ 30 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን ለሀገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ እንደኾነ ነው ሥራ አሥኪያጁ የተናገሩት።
በቀጣይ የተለያዩ የሀገር ውስጥ ገበያ አማራጮችን በመጠቀም እና 700 ሺህ የሚኾኑ አልባሳትን በማምረት ወደ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ ስለመኾኑም አንስተዋል። ወደ ወጭ ገበያ ለመግባትም የአሜሪካ እና የአውሮፓ መመዘኛ መስፈርቶችን እያሟላ እንደሚገኝ ነው ያመላከቱት።
ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ በቀን 28 ሺህ አልባሳትን በጥራት የማምረት ዓቅም አለው። ቲሸርት፣ ጅንስ፣ ሸሚዝ፣ የስፖርት ትጥቅ፣ የካኪ ልብሶችን፣ እና የመሳሰሉ አልባሳትን በጥራት ያመርታል። በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ ከ2ሺህ 500 እስከ 3ሺህ ቋሚ ሠራተኞች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ሥራ አሥኪያጁ ተናግረዋል።
የክልሉንም ይሁን የፌዴራል የጸጥታ አካላትን የደንብ ልብሶች ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ ማምረት እንደሚችል ሥራ አሥኪያጁ አረጋግጠዋል። ከውጭ ከማሥገባት ይልቅ ፋብሪካው እንዲያቀርብ ዕድል ቢሰጠው በጥራት ማቅረብ እንደሚችል ነው የተናገሩት።
የልማት ድርጅቶች ከፋብሪካው ጋር አብረው እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል።
በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ የኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ ፋሲል ዘውዱ አሁን ላይ በከተማዋ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በከተማዋ 110 አምራች ኢንዱስትሪዎች በሥራ ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል። በችግር ውስጥም ኾነው ፋብሪካዎች ሰፊ ምርቶችን እያመረቱ መኾኑንም አመላክተዋል።
በ2018 በጀት ዓመት እስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ ድረስ ከ5 ሺህ 213 ቶን በላይ ምርቶች ለውጭ ገበያ ኤክስፖርት መደረጉን ለአብነት አንስተዋል። ከ117 ሺህ 887 በላይ ቶን ተኪ ምርቶችን ማምረት መቻሉንም አስታውቀዋል።
ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ፣ ብድር እንዲያገኙ የማድረግ እና የግብዓት ችግሮች እንዲፈቱ የድጋፍ እና ክትትል ሥራዎች እየተሠሩ ስለመኾኑም አብራርተዋል።
ዓባይ ጋርመንት ከፍተኛ የሥራ ዕድል በመፍጠር አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ ትልቅ አቅም ያለው ፋብሪካ መኾኑን ቡድን መሪው ጠቁመዋል።
ምርታቸው እንዲተዋወቅ እና የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው በመድረኮች በማሳተፍ እና እንዲጎበኝ በማድረግ የከተማ አሥተዳደሩ እገዛ እያደረገ ስለመኾኑም አንስተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
