የኩላሊት ጠጠር ሕመምን እንዴት መከላከል ይቻላል ?

1
ባሕር ዳር: ኅዳር 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኩላሊት ጠጠር ብለን የምንጠራው ምን አይነት የሕመም ስሜት ሲሰማን ነው?
የኩላሊት ጠጠር ኩላሊት ውስጥ የሚሠራ በሰዎች የሥርዓተ ፍጭት ሂደት ሽንት በመመረት ሂደት ላይ የሚቀር ጠጣር አካል ነው። ከጥቃቅን ጠጣር አካል ወደ ከፍተኛ ጠጣራማነት የሚቀየር ጠጠር ነው፡፡ የኩላሊት ጠጠር ከኩላሊት እስከ ብልት ጫፍ ድረስ የትኛውም አካል ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረገ የኩላሊት ጠጠር ሕመም አጋጥሞት በሕክምና ተከታትሎ ያገገመ የ23 ዓመት ወጣት “ድንገት በጎኔ በኩል የውጋት ስሜት ተሰማኝ፤ ቀስ እያለ የሕመም ስሜቱ እየጨመረ እና በሆዴ አካባቢም የቁርጠት ስሜት እየተሰማኝ መጣ” ይላል።
ከዚያ በመቀጠል የምግብ ፍላጎቱ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነዱሱን፣ ምንም የመመገብ ፍላጎት እንዳልነበረው እና እንደምንም ብሎ ምግብ ሲቀምስ ደግሞ ያስታውከው እንደነበርም ገልጿል፡፡
ሕመሙ እየባሰ ሲመጣ በአቅርቢያ ከሚገኝ የሕክምና ተቋም በመሄድ ምርመራ እንዳደረገም አስረድቷል፡፡ በምርመራውም የኩላሊት ጠጠር መኾኑ እንደተነገው ገልጿል። ለተከታታይ ቀናት የሚወሰድ መድኃኒት በሐኪሙ ትዕዛዝ መሠረት መውሰድ እንደጀመረ አስታውሷል።
ጠጠሩን ጨርሶ ለማስወጣት እና እንዳይተካ ለማድረግም በየቀኑ ብዛት ያለው ፈሳሽ መውሰድ እንዳለበት እንደተነገረው ነው የገለጸው። ሐኪም የነገረውን ትእዛዝ በመቀበል የተሰጠውን መድኃኒት ሳያቆራርጥ በመውሰድ እና በየቀኑ ከሁለት ሊትር ውኃ ያላነሳ በመጠጣት ከሕመሙ ማገገም እንደቻለ ተናግሯል፡፡ አሁን ላይም ከሕመሙ አገግሞ በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።
የኩላሊት ጠጠር ከኩላሊት ውስጥ የሚሠራ በሥርዓተ ፍጭት ሂደት ውስጥ የሚገኝ ተረፈ ምርት ወይም ባዕድ ነገር ማለት ነው ያሉን በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኩላሊት ፊኛ እና ፕሮስቴት ቀዶ ሕክምና እና ሰብ ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር መኳንንት ይመር ናቸው፡፡
የኩላሊት ጠጠር እንዲከሰት የሚያደርጉ ቀጥተኛ ምክንያቶች የሉትም ያሉት ዶክተሩ ነገር ግን ብዙ አጋላጭ የኾኑ ምክንያቶች አሉ፤ ከእነዚህ ውስጥ እንደ መጀመሪያ ምክንያት የሚወስደው በቂ ፈሳሽ አለመውሰድ ነው ብለዋል። ከመጠን ያለፈ ጨው መጠቀምም ከምክንያቶቹ አንዱ ነው፡፡
ቁርጥማት፣ ግፊት፣ ስኳር፣ በሰውነት ላይ የቅባት መብዛት፣ ከሞቃታማ ሀገራት መኖር፣ ከመጠን በላይ የኾነ የእንስሳት ተዋጽኦዎችን መጠቀም (ከወተት ውጭ ያሉትን) የሽንት ኢንፌክሽን መኖር፣ በአጭር ወይም በረጅም ጊዜ የሚወሰዱ መድኃኒቶች ለኩላሊት ጠጠር ከሚያጋልጡ ምክንያቶች የተወሰኑት ናቸው ብለዋል፡፡
የኩላሊት ጠጠር በሁሉም የዕድሜ ክልል ላይ ያሉ ሰዎችን የሚያጠቃ ቢኾንም ባብዛኛው ከ30 እስከ 50 ዓመት እድሜ ክልል ያሉትን ያጠቃል ነው ያሉት፡፡ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ ከፍተኛውን ቁጥር ወንዶች ይያዛሉ፡፡
የኩላሊት ጠጠር መከሰቱን ከምንረዳባቸው መንገዶች ውስጥ በሽንጥ በኩል የሚሰማ የሕመመም ስሜት አንዱ ነው ይላሉ።
ኩላሊት ላይ የተሠራ ጠጠር በቱቦ በኩል አድርጎ እስከ ፊኛ እና ብልት ጫፍ ድረስ ሊሄድ ይችላል፡፡ በተለይ ቱቦ ውስጥ ገብቶ ከተቀረቀረ ከፍተኛ የኾነ ቁርጥማት፣ ማስታወክ፣ በየትኛውም አቅጣጫ ረፍት የማይሰጥ (በተለምዶ የወንድ ምጥ)እንደሚባለው ከበድ ያለ የሕመም ስሜት ይኖረዋል ነው ያሉት።
ጠጠሩ ኩላሊት ላይ ከኾነ ሕመሙ መካከለኛ የኾነ የመውጋት ምልክት ይኖረዋል፡፡ በልዩ ልዩ ኢንፌክሽኖች የሚፈጠር ከኾነ ደግሞ ሌሎችንም ምልክቶች እንደ ትኩሳት፣ ውጋት፣ ማስታወክ እና ማንቀጥቀጥ ያሉ ምልክቶች ሊታዩ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
በቱቦ በኩል አልፎ ወደ ፊኛ ሲጠጋ ደግሞ ቶሎ ቶሎ ሽንት ሽንት ማለት፣ የማቃጠል፣ ምቾት የሌለው ትንሽ ትንሽ ሽንት መሽናት ይኖረዋል፡፡ ሁሉም የጠጠር አይነቶች ደግሞ ምልክት ላይኖራቸው ይችላሉ ነው ያሉት፡፡ ጠጠሩ እንዳለበት አካባቢ ግን የሕመም ስሜቱ ይወሰናል ብለዋል።
ማንኛውም ሰው ከተቻለ የሕመም ስሜት ሳይሰማው በዓመት አንድ ጊዜ ጠቅላላ ሕክምና በማድረግ ጤንነቱን የማረጋገጥ ልምምድ ቢኖር ይመከራል ይላሉ። ካልተቻለ ሕመም ሲሰማን በቶሎ በአቅራቢያ ወደሌላ የሕክምና ተቋም በመሄድ በተለያዩ የሕክምና ዘዴዎች ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡
የኩላሊት ጠጠርን ለመከላከል በዋናነት በቂ ፈሳሽ መውስድ እና መነሻ ምክንያቱን በመለየት ማስተካከል እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
በቂ ፈሳሽ በመውሰድ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከ2 እስከ 2 ነጥብ 5 ሊትር ሊደርስ የሚችል ሽንት መሽናት ይገባል ነው ያሉት።
ይህ ማለት አንድ የኩላሊት ጠጠር ታማሚ በቀን ከ7 እስከ 8 ጊዜ ሽንት መሽናት ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ለኩላሊት ጠጠር አጋላጭ የኾኑ ምክንያቶችን ማስወገድ ይገባል ብለዋል።
እነዚህም የእንስሳት ተዋጽኦውን መጥኖ መውሰድ፣ በቂ የኾነ ፍራፍሬ መመገብ፣ ኢንፌክሽኖችን በጊዜው መታከም እና የሽንት ቀለምን በማየት በቂ የኾነ ፈሳሽ መውሰድ፣ በሞቃት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ሙቀቱ የሚፈጥረውን ከሰውነት የሚወጣ ፈሳሽን ሊተካ የሚችል በቂ ፈሳሽ መውሰድ፣ ተከታታይነት ያላቸው የሚወሰዱ መድኃኒቶችን ለይቶ መውሰድ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበኩር ጋዜጣን ያንብቡ
Next articleየብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀንን ማክበር ጠቀሜታው የጎላ ነው።