ቅርስን መጠበቅ የመንግሥት ብቻ ሳይኾን የሁሉም ማኅበረሰብ ድርሻ ነው።

1

ጎንደር: ኅዳር 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከጎንደር

አብያተ መንግሥታት ጥገና የተገኘውን ተሞክሮ በመውሰድ ሌሎች በአደጋ ውስጥ የሚገኙ ቅርሶችን መታደግ እንደሚገባ ጎብኝዎች ተናግረዋል።

 

አባ ሄኖክ የጎንደር አብያተ መንግሥታትን ሲጎበኙ ያገኘናቸው አባት ናቸው። በጎንደር የተለያዩ ጎብኝዎች በጥምቀት እና በሌሎች ጊዜያት በመምጣት በቅርሶቿ ተደንቀው፣ በከተማዋ ተደስተው፣ መንፈሳቸውን አድሰው፣ የጎንደርን የሥልጣኔ ዘመን እና የኢትዮጵያን ከፍታ ተረድተው እንደሚመለሱ አንስተዋል።

 

በቅርሶቹ ላይ የተደረገው ጥገና ዘመን ተሻጋሪ እንዲኾን ዕድል የፈጠረ እና የሚያስደንቅ መኾኑንም ተናግረዋል።

 

ቅርሱ ከጥገና በፊት ከከፍታው ወርዶ እና የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበት እንደነበር የተናገሩት ደግሞ አቶ ብርሃኑ ፍላቴ ናቸው። ቅርሱ ጥገና ሳይደረግለት ቢጎዳ ኑሮ ማንነታችን እና ባሕላችንን በማጣት የታሪክ ተወቃሽ እንኾን ነበር ነው ያሉት።

 

ታላላቅ ቅርሶቻችን የከፍታችን መገለጫዎች ናቸው ብለዋል። መንግሥት ቅርሱን ለመጠገን ያደረገው ተግባር የሚያስመሰግነው እንደኾነም አንስተዋል። የአብያተ መንግሥታቱ ጥገና የሚያኮራ መኾኑንም ተናግረዋል።

 

ቅርሱን መጠበቅ የመንግሥት ብቻ ሳይኾን የሁሉም ማኅበረሰብ ድርሻ መኾኑን ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ ለዘላቂነቱ ጥበቃ እንዲያደርግም አሳስበዋል።

 

ከቅርስ ጥገናው የተገኘውን ተሞክሮ በመውሰድ ሌሎች ቅርሶችን መንከባከብ እና መጠበቅ ይገባልም ብለዋል።

 

ዘጋቢ :- ያየህ ፈንቴ

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተፈራ ኀይሉ አጠቃላይ ሆስፒታል ማስፋፊያ ግንባታ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ተጠየቀ።