
ሰቆጣ: ኅዳር 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰቆጣ ከተማ የሚገኘው የተፈራ ኀይሉ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል የእናቶች እና ሕጻናት ሕክምና ማስፋፊያ ግንባታ ከተጀመረ ስምንት ዓመታትን አስቆጥሯል።
የሆስፒታሉ የማስፋፊያ ግንባታ መዘግየቱ ለእናቶች እና ሕጻናት የሚሰጠውን አገልግሎት ፈትኖታል።
በግንባታ ሥራው የተሰማሩ ባለሙያዎች ሥራውን ለማጠናቀቅ በጥራት እና በፍጥነት እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የተፈራ ኀይሉ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አሥኪያጅ ታምሩ ቢምረው በተፈራ ኀይሉ ሆስፒታል ባለው የክፍል ጥበት ምክንያት ለእናቶች እና ለሕጻናት አገልግሎት ለመስጠት እየተቸገሩ መኾኑን ተናግረዋል።
የግንባታው መጠናቀቅ የሆስፒታሉን መሠረታዊ ችግር የሚያቃልል መኾኑንም አብራርተዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ አሰፋ ነጋሽ የሆስፒታሉ ማስፋፊያ ግንባታ እስከ ጥር 2018 ዓ.ም ድረስ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲኾን የታቀደ ፕሮጀክት መኾኑን ተናግረዋል።
ይሁን እንጅ ግንባታውን ለማጠናቀቅ የሚረዱ ግብዓቶች አለመግባት እና የተጠናከረ የሰው ኀይል ይዞ ያለመሥራት ችግሮች እንዳሉም ጠቁመዋል። ይህም በቀሪ ሁለት ወራት ሥራው እንዳይጠናቀቅ ሊያደርገው ይችላል ነው ያሉት።
ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው የመቅደላ አምባ ኮንስትራክሽን በጥራት እና ፍጥነት ለማጠናቀቅ በትኩረት እንዲሠራም ጠይቀዋል።
ግንባታው 79 በመቶ ደርሷል ያሉት ደግሞ በመቅደላ አምባ ኮንስትራክሽን የተፈራ ኀይሉ ሆሰፒታል የእናቶች እና ሕጻናት ሕክምና ማስፋፊያ ፕሮጀክት ማናጀር ብርሃኑ አስራት ናቸው።
የጸጥታ ችግር እና የዶላር ምንዛሬ እጥረት ከውጭ በሚገቡ ጥሬ እቃዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳሳደረባቸውም ጠቁመዋል።
በቀሪ ወራትም ግንባታውን ለማጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ዘጋቢ ፦ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
