
ደብረ ማርቆስ: ኅዳር 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ወረዳ ሰብሸንጎ አለቅታም ቀበሌን ከበርጭ ወርቅ አንባ ቀበሌ የሚያገናኝ በሙጋ ወንዝ ላይ የተገነባው ተንጠልጣይ ድልድይ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾኗል።
ክረምት በመጣ ቁጥር የሰው እና የእንስሳት ሕይዎትን በመቅጠፍ የሚታወቀው ሙጋ ወንዝ መሸጋገሪያ ድልድይ ባለመኖሩ ወደ አጎራባች ቀበሌ ተጉዘው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮችን ለማከናወን ለረጅም ዓመታት ሲቸገሩ መቆየታቸውን የአካባቢው ነዋሪወች ተናግረዋል።
አሁን ላይ ችግሩ በመፈታቱ የዕለት ከዕለት ሥራቸውን ያለስጋት ለማከናወን እንዳስቻላቸው ነው የገለጹት።
ተንጠልጣይ ድልድዩ ለፍጻሜ እንድዲደርስ ብርቱ ጥረት ማድረጋቸውን የተናገሩት ነዋሪዎቹ ድልድዩ ረጅም ዓመታት አገልግሎት እንዲሰጥ ጥበቃ እና እንክብካቤ እንደሚያደርጉም ነው የተናገሩት፡፡
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የምሥራቅ ጎጃም ዞን መንገድ መምሪያ ኀላፊ ማናየ አዳነ የማኅበረሰቡ የዘመናት ጥያቄ የነበረው የሙጋ ወንዝ ተንጠልጣይ ድልድይ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ ለምረቃ መብቃቱን ገልጸዋል።
ግንባታው እንዲጠናቀቅ መንግሥት እና የአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን የጠቆሙት ኀላፊው ማኅበረሰቡ ድልድዩን በኀላፊነት እንድጠቀምም አሳስበዋል።
የደጀን ወረዳ ምክትል አሥተዳዳሪ ዘለቀ ደምሰው ድልድዩ በመንግሥት፣ በሄልቬታስ ኢትዮጵያ ግብረ ሰናይ ድርጅት እና በማኅበረሰብ ተሳትፎ በተገኘ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር እንደተገነባ ተናግረዋል።
የሙጋ ወንዝ ድልድይ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ከማጠናከር በዘለለ አጎራባች ቀበሌዎች ተገናኝተው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግባራትን ያለስጋት እንዲያከናውኑ ፋይዳው የጎላ በመኾኑ ማኅበረሰቡ ድልድዩን ተረክቦ በጥንቃቄ ማሥተዳደር ይጠበቅበታል ብለዋል።
ሕዳሴ ደብረ ብርሃን ገጠር መንገድ ኮንስትራክሽን ሽርክና ማኅበር በተባለ ተቋራጭ ድርጅት የተገነባው ተንጠልጣይ ድልድይ 75 ሜትር ርዝመት ያለው ሲኾን “ከ26 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ” ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
