
ጎንደር: ኅዳር 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የፋሲል አብያተ መንግሥታት ጥገና ቅርሶች ተጠብቀው ለመጭው ትውልድ እንዲተላለፉ ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር ጎንደር ከተማን ያስዋበ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል።
ከተቆረቆረች ከ400 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረችው ጎንደር ከተማ ለ250 ዓመታት የኢትዮጵያ መዲና ኾና ቆይታለች።
ጎንደር ከ1628 ዓ.ም ጀምሮ ለ250 ዓመታት የአጼዎች መናገሻ በመኾን የምትታወቅ እና የዓለም ታዋቂ የታሪክ ተመራማሪዎችን የምትስብ ውብ ከተማ ናት።
የዘመኑ አጼዎች የገነቧቸው ቤተ መንግሥታት እና አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም ሌሎችም ቅርሶች የከተማዋን እና የኢትዮጵያን ታሪክ ለዓለም ጥሩ ገጽታ በማላበስ የተመሠከረላቸው ናቸው።
ከተለያዩ ክፍለ ዓለማት ለጉብኝት እና ታሪክን ለመቃኘት የሚመጡ ጎብኝዎችን ቀልብም ይስባሉ።
በግዙፉነቱ እና በማራኪ አቀማመጡ የብዙዎችን ቀልብ የሚስበው የጎንደር አብያተ መንግሥታት ቅርስ ዕድሜ ጠገብ በመኾኑ የተለያዩ ጉዳቶችን አስተናግዶ ቆይቷል።
መንግሥት ለቅርሱ በሰጠው ትኩረት ጥገና በመደረጉ የቅርሱን የመፍረስ አደጋ መታደግ እንደተቻለ የተናገሩት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ማርያም ካሳሁን ናቸው።
የቅርሱ ጥገና እና በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማቶች፤ የአዘዞ መንገድ፤ የመገጭ ግድብ እና ሌሎች የልማት ሥራዎች የጎንደርን የመነሳት ዘመን የሚያበስሩ እና ከፍታዋን የሚመልሱ መኾናቸውንም ኀላፊዋ አንስተዋል።
የቅርሱ ጥገና እና በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ ልማቶች ከተማዋን የሚያስውቡ፤ የጎብኝዎችን ቁጥር የሚጨምሩ፤ የጎብኝዎችን ምቾት የሚጠብቁ እና በአጠቃላይ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ይበልጥ የሚያሳድጉ መኾኑን ነው የተናገሩት።
“ጎንደር ከመሞሸር ባለፈ ወደ ከፍታዋ እንድትመጣ የቅርስ እድሳቱ የሚኖረው ሚና የጎላ መኾኑን” ያነሱት መምሪያ ኀላፊዋ በቀጣይ የጎብኝዎችን ቆይታ የሚያራዝሙ ተግባራትን ለማከናወን ይሠራል ነው ያሉት።
የቅርሱ ጥገና ታሪክን እና ሥልጣኔን ማንሳት፣ ማሳወቅ እና ማስተላለፍ መኾኑ ታምኖበት የተሠራው ተግባር የሚያስደንቅ ስለኾነ በቅርሱ እድሳት እና በከተማዋ ልማት እየተሳተፉ ለሚገኙ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
