የኢትዮጵያ የጸረ ድህነት ትግል እና የግብጽ ሴራ

2

ባሕር ዳር: ኅዳር 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያ የቀደመ የሥልጣኔ እና የገናናነት ታሪክ ባለቤት ናት። የገናና ሥልጣኔ ባለቤት የኾነችው ኢትዮጵያ በጠላቶች ሴራ እና በሌሎች ችግሮች በታሪኳ ልክ ሀብታም ሳትኾን ቆይታለች።

የውጭ ጠላቶች እና የውስጥ ግጭት ጠማቂዎች ኢትዮጵያ እንዳታድግ አድርገዋት ኖረዋል። ከውጭ ሴረኞች እና የኢትዮጵያን እድገት በክፋት ከሚመለከቱ ሀገራት መካከል ደግሞ ግብጽ ቀዳሚዋ ናት።

ግብጽ በኢትዮጵያ በቀጥታ ጦርነት፣ ሌሎች ጦርነቶችን በመደገፍ እና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉ ግጭቶችን እና አለመረጋጋቶችን በማባባስ ስታሴር ኖራለች። አሁንም ከሴራ የምትቦዝን ሀገር አይደለችም።

ግብጽ ዓባይን በብቸኝነት ለመጠቀም ካላት ፍላጎት የተነሳ በኢትዮጵያ ላይ የማትሸርበው ሴራ እንደሌለ እና የሌት ከቀን ሥራዋ መኾኑንም ታሪክ ይነግረናል፡፡ ግብጽ በውስጥም ኾነ በውጭ ፖሊሲዋ የዓባይ ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳዋ ነው።

ተፈሪ መኮነን (ዶ.ር) “የዓባይ ውኃ ጉዳይ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ግብጽ የዓባይ ውኃን በብቸኝነት ለመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ የምትሸርበውን ሴራ ጽፈዋል።

ግብጽ ለሴራዋ ይመቻት ዘንድ ሱዳን የአረብ ሊግ አባል እንድትኾን ረድታለች። በዚህም የዓባይ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራትን ለመሞገት ስትራቴጅክ አጋር አስገኝቶላታል። ግብጽ ከሊቢያ ጋር በመተባበር የአፍሪካ እንድነት ጽሕፈት ቤትን ከአዲስ አበባ እናስወጣለን የሚል ሴራም ሸርባ ነበር ይላሉ። ግብጽ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሁሉ ስትፈታተን እንደኖረችም ከትበዋል።

የግብጽ መንግሥታት ከሕዝባቸው መግባቢያ እና መተሳሰሪያቸው፤ በሥልጣን የሚያቆያቸውም ዓባይን ከኢትዮጵያ ነጥቆ የግብጽ ብቻ የማድረግ ጉዳይ ነው። ሕዝቡም መንግሥታቶቹን ከሚለካባቸው መስፈርቶች ውስጥ ዋናው ዓባይን የግብጽ ብቻ የማድረግ ጉዳይ ይመስላል። የደርግ የፖለቲካ ርዕዮተዓለም፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና በዓባይ ተፋሰስ ላይ ያደረገው የመስኖ አዋጭነት ጥናት ግብጽ እና ሱዳን እንደገና በኢትዮጵያ ላይ እንዲዘምቱ እንዳደረጋቸውም ጽፈዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ሰላማዊ ጉርብትና እንዳይኖራት ግብጽ የቻለችውን ሁሉ ታሴራለች።

የደርግ መንግሥት ”ወንዞች ይገደቡ ይዋሉ ለልማት፣ በከንቱ ፈስሰዋል ለብዙ ሺ ዓመታት” በሚል መዝሙር ታጅቦ ዓባይን እና ሌሎች ወንዞችን ለመስኖ ለመጠቀም ”አረንጓዴ” ዘመቻ ማድረጉ ግብጽን አስደንግጦ ነበር።

በዚህም ከሚዲያ ፕሮፓጋንዳ እስከ ዲፕሎማሲያዊ ሴራ እና የጦርነት ዛቻ እንደገና አስቀጥላለች፡፡ ከእስራኤል ጋር የነበራትን ቅራኔ በካምፕዴቪድ ስምምነት ያለዘበችው ግብጽ ሙሉ ትኩረቷን በዓባይ የበላይነት እና በኢትዮጵያ ላይ አድርጋ ነበር።

አንዋር ሳዳት ግብጽ ከእስራኤል ጋር በፈጠረችው የሰላም ስምምነት መሠረት ፋታ ማግኘት ብቻ ሳይኾን የሀገሯ ውስጥ የሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት የሲናይ ምድረ በዳን የማልማት ዕቅድ ይፋ አድርገዋል፡፡ ከዚህም አልፎ በ1979 ዓ.ም የዓባይን ውኃ ለእስራኤል ለመስጠት ቃል ገብተዋል፡፡ የውኃ ፖለቲካውን በማወሳሰብ ኢትዮጵያን መብለጥ ብቻ ሳይኾን ከሌሎች ሀገራትም የምትጣላበት ሴራ ተሸርቦ ነበር፡፡

በዚህም ከተፋሰሱ ውጭ የኾነችው እስራኤል የዓባይ ውኃ በግብጽ በኩል እንዲደርሳት እና በይገባኛል ስሜት ጸረ ኢትዮጵያ አቋም እንዲኖራት የተሄደበትን ርቀት ያጤናል፡፡ ግብጽ የትኛውም የትብብር ማዕቀፍ የኢትጵያን ልማት የሚደግፍ ከኾነ ከማንኛውም ኀያል እና ሀገር ቢኾን በዲፕሎማሲም ኾነ በሴራ ፍጥጫ ውስጥ እንደምትገባ ያመላክታሉ፡፡ ለዚህም ነው በግብጽ ወደ ሥልጣን ለመውጣት፣ በሥልጣን ለመቆየት እና የሕዝብ አመጽ ለማለዘብ ዓባይን በሀብትነት፤ ኢትዮጵያን በጠላትነት ማንሳት ካርድ ተደርጎ የሚመዘዘው፡፡

ኢትዮጵያ ለዓባይ 85 በመቶ ማበርከቷ ብቻ ሳይኾን ካላት መብት ፣ ከታሪካዊ፣ ከጂኦግራፊዊ እና ከቀጣናው ፖለቲካዊ ዳራዋ አኳያ ግብጽ በእጅጉ ትፈራታለች፡፡ ለዚያም ነው የተረጋጋ ሰላም እንዳይኖራት፤ ሙሉ አቅሟን በልማት ላይ እንዳታውል አብዝታ የምታሴርባት፡፡

ግብጽ ምንም ያህል ብታሴር እና ጥፋት ብትጠነስስ ኢትዮጵያውያን ድህነት አስመርሯቸው፣ ተረጅነት አስቆጭቷቸው በቁርጠኝነት እና በአንድነት ከተነሱ የግብጽ ማንኛውም ሴራ ሊያስቀራቸው እንደማይችል በታላቁ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ማየት ይቻላል፡፡

አሁን ላይ የዓባይ ውኃ ፖለቲካ እንደ ድሮው አለመኾኑን የጠቀሱት ዶክተር ተፈሪ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ለመብታቸው እየታገሉ መኾኑን እና ኢትጵያም ብቻዋን አለመኾኗን ያነሳሉ፡፡ ይህም ለኢትዮጵያ ሌላ አቅም ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን እንዲለያዩ እና እንዲዳከሙ የሚደረግባቸውን ሴራ እና ጣልቃ ገብነት አለማስተናገድ፣ ችግሮቻቸውን በውይይት መፍታት፣ በዕለታዊ ኩርፊያ የጠላት መሳሪያ አለመኾን ይጠበቅባቸዋል ነው የሚሉት።

የለማች እና ጠንካራ ኢትዮጵያን የማትፈልገው ግብጽ በተጀማመሩ ፕሮጀክቶች ደስተኛ አትኾንም፡፡ በዲፕሎማሲ አሻጥር፣ በዓለም መድረኮች የማይገባ ጥያቄ ከማቅረብ እና ግጭቶችን ከመጥመቅ አትቦዝንም፡፡ ኢትዮጵያውያንም ይህንን በመገንዘብ ከልማታቸው የሚያደናቅፉቸውን ሁሉ መቀበል የለባቸውም ነው የሚሉት።

የውስጥ አንድነታቸውን በማጠናከር፣ የሚሸረቡባቸውን ሴራዎች ሁሉ እየበጣጠሱ ወደ እድገት ማማ መውጣት አለባቸው። ኢትዮጵያውያን አንድ ሲኾኑ ማንም እንደማይደፍራቸው፤ የማንም ሴራ እንደማያስቆማቸው ታሪክ ምስክር ነው። የዚህ ዘመን የአንድነታቸው ውጤት የሕዳሴ ግድብም ሕያው አብነት ነው።

ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን በተለያዩ ኹነቶች ለማክበር ዝግጅት አድርጓል።
Next article10ኛው የከተሞች ፎረም የቅድመ ዝግጁት ሥራ መጠናቀቁን የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትቴር አስታወቀ።