
ጎንደር: ኅዳር 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር አብያተ መንግሥታትን ስትጎበኝ ያገኘናት የጎንደር ከተማ ነዋሪዋ ፋሲካ በጋሻው ቅርሱ የተደረገለት ጥገና የግቢውን ውበት ያሳመረ፣ ለጎብኝዎች ምቾትን የሰጠ መኾኑን አንስታለች።
የጎንደር አብያተ መንግሥታት ጥገና የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ የሚያራዝም እና ከተማዋ ከቱሪዝም የምታገኘውን ጥቅም የሚያሳድግ መኾኑንም ጠቅሳለች።
ሌላው ተማሪ እያለ ወደ ቤተ መንግሥቱ በመምጣት ይጎበኝ እንደነበር እና ያኔ ቅርሱ የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበት እንደነበር ትዝታውን ያጫወተን ወጣት ታዘብ አያሌው ነው። አሁን ላይ የቅርስ ጥገናው የሚያስደስት እና ከመፍረስ የታደገ መኾኑን ገልጿል።
ጎንደር በሥልጣኔ ዘመኗ አልቆና አርቆ አሳቢ በኾኑ መሪዎች የኪነ ሕንጻ፣ የሥነ ጽሑፍ እና የሥነ ስዕል ጥበብን በማሳደግ ለትውልድ የሚያኮራ ቅርስን አስቀምጠው ማለፋቸውን የጎንደር ከተማ አስጎብኝዎች ማኅበር አባል ሙሉቀን ተገኘ አብራርቷል።
የቅርስ ጥገናው የጎንደር ሥልጣኔ ዳግም እንዲመለስ እድል የፈጠረ መኾኑን አንስቷል። ለጎንደር ዳግም መነሳት ሁሉም የድርሻውን መወጣቱን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቋል።
በቅርሱ ላይ የተደረገው ጥገና እና በከተማዋ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ጎብኝዎች ቆይታቸው እንዲራዘም እና በከተማዋ ተዘዋውረው ምቹ ጊዜያትን እንዲያሳልፉ እድል እንደሚፈጥርም አስጎብኝው ተናግሯል።
ጥገና ከመደረጉ በፊት አብዛኛዎቹ ቅርሶችን ወደ ውስጥ ገብቶ ለማስጎብኘት እና ለመጎብኘት የማይቻል እንደነበር አስታውሷል። በተደረገለት ጥገና አሁን ላይ ጎብኝዎችን አብያተ መንግሥታቱ ውስጥ በማስገባት ለማሳየት እና ታሪኩን ለማስረዳት ይበልጥ እድል የፈጠረ መኾኑን አንስቷል።
በኮሮና ቫይረስ፣ በሰሜኑ ጦርነት እና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የቱሪዝም እንቅስቃሴው ተዳክሞ እንደነበር ያስታወሰው አስጎብኝው አሁን ላይ የአብያተ መንግሥታቱን ታሪክ ይበልጥ ለጎብኝዎች ለማሳወቅ እንደሚሠሩም ተናግሯል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
