የአማራ ክልል የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን በተለያዩ ኹነቶች ለማክበር ዝግጅት አድርጓል።

6
ባሕርዳር፡ ኅዳር 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልዕክት የሚከበረውን 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ክልላዊ ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ከፍያለው ማለፉ በየዓመቱ ኅዳር 29 የሚከበረው የኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር ከጀመረበት ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ የሕዝቦችን አብሮት ለማሳደግ በሚያስችል መልኩ እየተከበረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
ዘንድሮም ከኅዳር 01 እስከ 29/2018 ዓ.ም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ በሕገ መንግሥት፣ በፌደራሊዝም አስተምህሮዎች እና በሌሎች ኹነቶች በክልሉ እንደሚከበር ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል በብዝኀነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ሥር እንዲሰድ እና እንዲዳብር በማድረግ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጎልበት የበዓሉ ዋና ዓላማ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡ ቀኑን ምክንያት በማድረግ የሚከናወኑ ኹነቶች እቅድ ተዘጋጅቶላቸው እና ኮሚቴዎች ተዋቅረው ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ክልል አቀፍ የመክፈቻ ፕሮግራሙ ኅዳር 05/2018 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ በደመቀ ሁኔታ በይፋ እንደሚካሄድም ተናግረዋል።
የሚከናወኑ ኹነቶች በአራት ሳምንታት የተከፋፈሉ መኾናቸውንም ጠቅሰዋል።
ከኅዳር 01 እስከ 07/2018 ዓ.ም ያለው የመጀመርያው ሳምንት በሁሉም የክልሉ አካባቢ የአስተምሮ ሥራዎች የሚከወኑበት የአስተምሮ ሳምንት ተብሎ መሰየሙን ነው የገለጹት። በዚህም 3 ሚሊዮን የሚኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ እንዲኾኑ ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በሁለተኛው ሳምንት ደግሞ ድጋፍ ለሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ የማጋራት፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት የመጠገን፣ የደም ልገሳ፣ በክረምት የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ እና የከተማ ጽዳት ይሠራል ነው ያሉት።
በኅዳር ሦሥተኛ ሳምንት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ተግባራት የማጠናከርያ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ነው የተናገሩት። በዚህም በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ ወረዳዎች፣ ዞኖች እና ከአጎራባች ክልሎች ጋር ግንኙነትን የሚያጎለብቱ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ነው የጠቀሱት። የልማት ሥራዎች ጉብኝት፣ የባሕል አልባሳት እና እቃዎች አውደ ርዕይ እንደሚኖርም አንስተዋል።
ከኅዳር 23 እስከ 29/2018 ዓ.ም ባለው አራተኛው ሳምንት ክልላዊ የማጠቃለያ ፕሮግራም በደብረ ብርሃን ከተማ እንደሚካሄድ ተናግረዋል። የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበትም ሲምፖዚየምን ጨምሮ በልዩ ልዩ የባሕል ትርኢቶች እንደሚጠቃለልም ገልጸዋል።
በመጨረሻም ኅዳር 29/2018 ዓ.ም ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እና የሕዝብ ተወካዮች በተገኙበት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ሀገር አቀፍ የማጠቃለያ ፕሮግራም እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ልዑክም ከሌሎች አካባቢ ወንድም እና እህት ሕዝቦች ጋር የማኅበራዊ አኗኗር፣ ልምዶች እና የአለባበስ ባሕልን በማሳየት ብዝኀነት ውበት መኾኑን እና ለኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ሥርዓት መጽናት እና መረጋገጥ ሚናውን ይወጣል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየወባ በሽታ ሥርጭት ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር መቀነሱን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ።
Next articleየኢትዮጵያ የጸረ ድህነት ትግል እና የግብጽ ሴራ