
ደብረ ማርቆስ: ኅዳር 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች በየሳምንቱ የወባ በሽታን ለመከላከል ማኅበረሰብን ያሳተፈ የአካባቢ ቁጥጥር ተግባራትን እያከናወነ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ አስታውቋል።
በተከናወነው የቅድመ መከላከል ተግባር የወባ በሽታ ሥርጭት ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱንም መምሪያው ገልጿል።
በደጀን ወረዳ የወባ በሽታ ሥርጭትን ለመከላከል ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በመቀናጀት የአካባቢ ቁጥጥር እና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን የተናገሩት የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት የወባ መከላከል ባለሙያው ጌቴ አበረ ናቸው።
በወረዳው ለወባ መራቢያ የኾኑ ቦታዎችን ሲያጸዱ ያገኘናቸው ነዋሪዎችም የወባ በሽታ በተለይም በእናቶ እና ሕጻናት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በየሳምንቱ አካባቢን የማጽዳት ተግባር እያከናወኑ መኾኑን ነግረውናል።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን የወባ በሽታ የማኅበረሰቡ የጤና ችግር እንዳይኾን ከአካባቢ ቁጥጥር ተግባር ባሻገር ቤት ለቤት ህክምናን ተደራሽ የማድረግ ተግባር እና የአጎበር ሥርጭት መከናወኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ጤና መምሪያ ኅላፊ የሺዋስ አንዷለም ናቸው።
በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች በየሳምንቱ አርብ አርብ ማኅበረሰብን ያሳተፈ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ እየተከናወነ መኾኑን የገለጹት አቶ የሺዋስ በተከናወነው ቅድመ መከላከል ሥራ የወባ በሽታ ሥርጭት ከባለፈው ሩብ ዓመት አንጻር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን አስረድተዋል።
የወባ በሽታን ለመከላከል ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል የአካባቢ ቁጥጥር ተግባርን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
