
ባሕር ዳር: ኅዳር 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የግል ድርጅት ሠራተኞች የጡረታ ዋስትና ሠራተኞች ጡረታ ከወጡ በኋላ ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ ያግዛል። በእርጅና፣ በጤና ጉድለት ወይም በሞት ምክንያት የሚገጥማቸውን የገቢ መቋረጥ ስጋት ለመከላከል አስተዋጽኦ አለው።
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሕግ ባለሙያ ደመቀ ይብሬ በኢትዮጵያ የግል ድርጅት ሠራተኞች የጡረታ ዋስትና የሚያገኙበት የሕግ ማዕቀፎች መኖራቸውን ይገልጻሉ። የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1268/2014 አንዱ መኾኑንም ጠቁመዋል።
በአዋጁ እንደተገለጸው የግል ድርጅት ሠራተኛ የሚባለው በግል ድርጅት ውስጥ ከ45 ቀናት ላላነሰ ጊዜ ደመወዝ እየተከፈለው ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ የተቀጠረ ሠራተኛ ማለት ነው።
የግል ድርጅት ማለት ለንግድ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለእርሻ፣ ለኮንስትራክሽን፣ ለማኅበራዊ አገልግሎት ወይም ለሌላ ሕጋዊ ዓላማ የተቋቋመ፣ ሠራተኛ ቀጥሮ ደመወዝ እየከፈለ የሚያሠራ የግል ተቋም ወይም ሰው እንደኾነ በአዋጁ ተመላክቷል።
ማንኛውም የግል ድርጅት ሠራተኛው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቀጠር የሞላውን የግል መረጃ፣ የአገልግሎት እና የቤተሠብ ሁኔታ መግለጫ፣ የተሰጠውን የቅጥር ደብዳቤ እና ሌሎች መረጃዎችን ለግል ድርጅት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አሥተዳደር በማቅረብ ማስመዝገብ እንዳለበት አብራርተዋል፡፡
አዲስ የተቋቋመ የግል ድርጅት ወይም አዲስ የተቀጠረ ሠራተኛ ድርጅቱ በተቋቋመ ወይም ሠራተኛው በተቀጠረ በ60 ቀናት ውስጥ ምዝገባውን ማከናወን እንደሚኖርበት ያስረዳሉ፡፡
ማንኛውም የግል ድርጅት የራሱን እና የሠራተኛውን የምዝገባ መረጃ ለውጥ ሲያጋጥም በ6ዐ ቀናት ውስጥ ለአሥተዳደሩ በማቅረብ ማሳወቅ እንደሚጠበቅም በአዋጁ ተቀምጧል፡:
በአዋጁ እንደተገለጸው ለግል ድርጅት ሠራተኞች አገልግሎት ጡረታ ፈንድ በሠራተኛው ደመወዝ ላይ ተመስርቶ የሚደረገው የጡረታ መዋጮ በግል ድርጅቱ 11 በመቶ፤ በግል ድርጅት ሠራተኛው ደግሞ 7 በመቶ ይኾናል፡፡
ማንኛውም የግል ድርጅት የሠራተኞች የጡረታ መዋጮ ከደመወዛቸው ቀንሶ እና የራሡን መዋጮ ጨምሮ ለጡረታ ፈንዱ በየወሩ የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ ከሠራተኞቹ ደመወዝ ሊቀነስ የሚገባውን መዋጮ ሳይቀንስ የቀረ የግል ድርጅት ክፍያውን ራሱ ለመፈፀም እንደሚገደድ አብራርተዋል፡፡
የግል ድርጅት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ፈንድ አሥተዳደር ወይም ውክልና የተሠጠው አካል ተገቢውን የጡረታ መዋጮ ለጡረታ ፈንድ ገቢ ሳያደርግ ከሦሥት ወር በላይ የቆየ የግል ድርጅትን በባንክ ወይም በፋይናንስ ተቋም ካለው ሂሣብ ላይ ተቀንሶ ገቢ እንዲኾን የማስደረግ ሥልጣን ይኖረዋል፡፡
የግል ድርጅት ሠራተኛው የአገልግሎት ዘመን መቆጠር የሚጀምረው በሠራተኛነት ተቀጥሮ በጡረታ ዕቅድ ከተሸፈነበት ቀን ጀምሮ እንደኾነ የሕግ ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡
የግል ድርጅት ሠራተኛው በመንግሥት ሠራተኞች ጡረታ ዕቅድ በሚሸፈን የመንግሥት መሥሪያ ቤት የፈጸመው አገልግሎት በዕቅዱ መዋጮ መክፈል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እንደሚያዝ አብራርተዋል፡፡
የግል ድርጅት ሠራተኛው የጡረታ ዕቅድ ሽፋን ባላቸው የግል ድርጅቶች የተፈጸመው የአገልግሎት ዘመን በሙሉ ተደምሮ እንደሚታሰብለትም ነው የገለጹት፡፡
የግል ድርጅት ሠራተኛው የደመወዝ ክፍያ ሳይቋረጥ በማናቸውም ምክንያት አገልግሎቱ ተቋርጦ የቆየበት ጊዜ፣ በየወሩ ደመወዝ እየተከፈለው ሙሉ ጊዜውን በማናቸውም የመንግሥት አካል በሕዝብ ወይም በሠራተኛ ማኅበር በተመራጭነት አገልግሎት የሰጠበት ጊዜ፤ ልዩ ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ኾኖ በመንግሥት ውሳኔ በዓለም አቀፍ ድርጅት በማገልገል ያሳለፈው ጊዜ በአገልግሎት ይታሰብለታል፡፡
የጡረታ መውጫ ዕድሜ የግል ድርጅት ሠራተኛው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቀጠር በቅድሚያ ያስመዘገበውን የልደት ዘመን መሠረት በማድረግ 60 ዓመት እንደኾነ የሕግ ባለሙያው አብራርተዋል፡፡
የጡረታ ፈንድ አሥተዳደሩ በሚያቀርበው ጥናት መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በልዩ ሁኔታ ለሚታዩ የሙያ መስኮች ከ60 ዓመት በላይ የኾነ የጡረታ መውጫ ዕድሜ ወይም ለጤንነት እና ለሕይወት አስጊ በኾኑ የሥራ መስኮች ላይ ለተሠማሩ የግል ድርጅት ሠራተኞች ከ60 ዓመት ያነሰ የጡረታ መውጫ ዕድሜ ሊወስን ይችላል፡፡
በአዋጁ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ለ1ዐ ዓመታት ያገለገለ ሠራተኛ የጡረታ መውጫ ዕድሜው በመድረሱ ከሥራ ሲሠናበት የአገልግሎት ጡረታ አበል እስከ ዕድሜ ልኩ ይከፈለዋል፡፡
ለ25 ዓመታት ያገለገለ ሠራተኛ በራሱ ፈቃድ ወይም በአዋጅ ከተጠቀሱት ውጭ በኾነ ምክንያት አገልግሎት ካቋረጠ የጡረታ መውጫ ዕድሜው ሊደረስ 5 ዓመታት ከሚቀረው ጊዜ ጀምሮ የአገልግሎት ጡረታ አበል እስከ ዕድሜ ልኩ ይከፈለዋል፡፡
ይህም ማለት የጡረታ መውጫ ዕድሜው 60 ዓመታት የኾነ የግል ድርጅት ሠራተኛ 25 ዓመት አገልግሎት ካለው በ55 ዓመቱ በራሱ ፈቃድ አገልግሎት ካቋረጠ የአገልግሎት ጡረታ አበል እስከ ዕድሜ ልኩ የማግኘት መብት አለው፡፡
የጡረታ መውጫ ዕድሜው ሳይደርስ በጤና ጉድለት ምክንያት ለሥራ ብቁ አለመኾኑ በሕክምና ከተረጋገጠ የአገልግሎት ጡረታ አበል እስከ ዕድሜ ልኩ ይከፈለዋል፤ የሞተ እንደኾነም ከሞተበት ጊዜ ቀጥሎ ካለው ወር ጀምሮ ለተተኪዎች አበል ይከፈላል፡፡
ለማንኛውም 10 ዓመታት ላገለገለ የግል ድርጅት ሠራተኛ የሚከፈለው የአገልግሎት ጡረታ አበል መጨረሻ ባገለገለባቸው ሦስት ዓመታት ውስጥ ይከፈለው የነበረው አማካይ ደመወዝ 30 በመቶ ኾኖ ከ10 ዓመታት በላይ ለፈጸመው ለእያንዳንዱ ተጨማሪ ዓመት አገልግሎት በ1 ነጥብ 25 በመቶ ተጨምሮ ይታሰባል፡፡
ከአሥር ዓመታት ያነሰ አገልግሎት ያለው የግል ድርጅት ሠራተኛ የጡረታ መውጫ ዕድሜው ከመድረሱ በፊት ከሥራ ሲሰናበት የአገልግሎት ጡረታ አበል እንደማይከፈለው የሕግ ባለሙያው ጠቁመዋል።
አሥር ዓመታት ያገለገለ የግል ድርጅት ሠራተኛ በጤና ጉድለት ምክንያት ሥራ መሥራት እንደማይችል ተረጋግጦ ከሥራ ሲሰናበት የጤና ጉድለት ጡረታ አበል እስከ ዕድሜ ልኩ ይከፈላል።
ማንኛውም የግል ድርጅት ሠራተኛ የተወሰነለትን የጡረታ አበል በወቅቱ መውሰድ አለበት። የውዝፍ ጡረታ አበል ክፍያ ጥያቄ ከአምስት ዓመታት በኋላ በይርጋ ይታገዳል፡፡
የያዘውን ማስረጃ በዚህ አዋጅ መሠረት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልኾነ ወይም የአዋጁን ድንጋጌ አፈጻጸም የሚያሰናክል ተግባር የፈጸመ ማንኛውም ሰው አግባብ ባለው የወንጀል ሕግ ድንጋጌ መሠረት እንደሚያስቀጣ የሕግ ባለሙያው አብራርተዋል፡፡
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
