የአየር ኀይል የኢትዮጵያ የታላቅነቷ እና ስመ ገናናነቷ ማሳያ ነው።

3

አዲስ አበባ: ኅዳር 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢ.ፌ.ዲ.ሪ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት ክብረ በዓልን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የአየር ኀይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ ኢትዮጵያ ታላቅ እና ጥንታዊት ሀገር ናት ብለዋል።

የታላቅነቷ መገለጫም አንዱ ከአፍሪካ እና ሌሎች ሀገራት ቀድማ ዘመናዊ ተቋማትን ማቋቋሟ መኾኑን ገልጸዋል።

የአየር ኀይል የታላቅነቷ እና ስመ ገናናነቷ ማሳያ ነውም ብለዋል። አየር ኀይል የኢትዮጵያን አንድነት እና አይደፈሬነት በደም እና በአጥንት መስዋዕትነት ያስጠበቀ ተቋም መኾኑንም ገልጸዋል።

ዛሬ ላይ 90 ዓመት እድሜ ላይ ደርሷል፤ አየር ኀይል በሥልጠና፣ በውጊያ እና ጥገና ዘመኑን የዋጁ ትጥቆችን ታጥቋል ነው ያሉት።በተቋማዊ ግንባታ፣ በሰው ኀይል በመሠረተ ልማትእና በትጥቅ ለኢትዮጵያ በሚመጥን መልኩ ራሱን እያበቃ ይገኛል ብለዋል።

ይህ ታሪካዊ እና ግዙፍ ተቋም በየዓመቱ በተለያዩ ዝግጅቶች ምሥረታውን እያከበረ ይገኛል። በዘንድሮው የምሥረታ ቀንም “ለአየር ኀይል ዕድገት በሙሉ አቅሜ እሮጣለሁ” በሚል መሪ መልዕክት ቢሾፍቱ ከተማ ዓለም አቀፍ የአስር ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ይካሄዳል ብለዋል። ከፍተኛ ሽልማት የሚያስገኘው ሩጫው ኅዳር 21/2018ዓ.ም እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

የሩጫ ውድድሩ አንዴ ብቻ የሚካሄድ ሳይኾን በየዓመቱ የቢሾፍቱ ከተማ ልዩ መለያ በመኾን የሚካሄድ ነው ብለዋል። ለውድድሩ አስፈላጊው ዝግጅቶች ተከናውነዋል፤ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ተቋም በኾነው የምሥረታ በዓል ተገኝቶ ለአየር ኀይል እንዲሮጥ ጥሪ አቅርበዋል።

የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ ዓለማየሁ አሰፋ “ለአየር ኀይል ዕድገት በሙሉ አቅሜ እሮጣለሁ” በሚል መሪ መልዕክት በቢሾፍቱ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የአስር ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት እና የጎብኝዎች ፍሰት መጨመር ምክንያት ነው ብለዋል።

የከተማ አሥተዳደሩ እና ነዋሪዎች በተለመደው እንግዳ ተቀባይነት በፍቅር ለመቀበል ተዘጋጅተዋል፤ ውድድሩን ማካሄድ የሚያስችል መሠረተ ልማቶች እና ግንባታዎች ተከናውነዋል፤ እንግዶች የሚያርፉባቸው እና የሚዝናኑባቸው ሆቴሎችን አቅምን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ለማስተናገድ ተዘጋጅተዋል ነው ያሉት።

የአየር ኃይል የምሥረታ በዓል ከኅዳር 20/2018ዓ.ም ጀምሮ በኢግዚቢሽን በዓይነቱ ልዩ በኾነ የአየር ላይ ትርኢት ይከበራል ተብሏል።

ዘጋቢ:- ኢብራሂም ሙሃመድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየግል ድርጅት ሠራተኞች የጡረታ መብት አላቸው?