
ጎንደር: ኅዳር 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር የሚመጡ ጎብኝዎችን በአግባቡ ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን የጎንደር ከተማ ዓለም አቀፍ ቅርስ አሥተዳደር አስታውቋል።
ጎንደር ከተማን ከሚያደምቋት በዓላት መካከል የጥምቀት በዓል አንደኛው ነው። ከተማዋ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን የያዘች መኾኗ ደግሞ ጎንደርን ተመራጭ ያደርጋታል።
አሁን ላይ የአብያተ መንግሥታቱ መጠገን የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም እንደሚያግዝ የጎንደር ከተማ አስጎብኝዎች ማኅበር አባል ሙሉቀን ተገኘ ተናግረዋል።
ወደ ታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ የሚመጡ ጎብኝዎችን በአግባቡ አስተናግዶ ለመሸኘት ዝግጁ መኾናቸውንም ነው የገለጹት።
ጎንደር ከተማን ከሌላው ጊዜያት ለየት የሚያደርጋት የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ የአብያተ መንግሥታቱ ጥገና መጠናቀቁ ነው ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ ዓለም አቀፍ ቅርስ አሥተዳዳሪ ጌታሁን ስዩም ናቸው።
ይህ መኾኑ ደግሞ ከተማዋን ልዩ ገጽታ አጎናጽፏታል ብለዋል። የጥምቀት በዓልን ተንተርሶ የሚመጡ ጎብኝዎችን በአግባቡ ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል።
የጎንደር አብያተ መንግሥታትን ለ24 ሰዓታት የማስጎብኘት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ :- አዲስ አለማየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
