
ጎንደር: ኅዳር 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከተቆረቆረች ከ400 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረችው ጎንደር ከተማ ለ250 ዓመታት የኢትዮጵያ መዲና ኾና ቆይታለች።
በሥልጣኔ ዘመኗ አብያተ መንግሥታትን ጨምሮ ሌሎች የቱሪዝም መዳረሻ ኪነ ሕንጻዎችን በመገንባት መንግሥታቱ የታሪክ አሻራቸውን አስቀምጠዋል። ቅርሶቹ በኪነ ሕንጻ ጥበባቸው እና አቅፈው በያዟቸው ታሪክ ከኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን አልፈው የዓለም ሃብት ኾነዋል።
ይሁን እንጅ ለበርካታ ዓመታት ተዘንግተው በመቆየታቸው የመፍረስ አደጋ ተጋርጦባቸው እንደነበር የጎንደር ዓለም አቀፍ ቅርስ አሥተዳደር አሥተዳዳሪ ጌታሁን ስዩም አንስተዋል።
አሁን ላይ መንግሥት ለጎንደር አብያተ መንግሥታት ቅርስ በሰጠው ትኩረት የቅርስ ጥገና በመደረጉ ወደ ቀደመ ክብሩ መመለሱንም አንስተዋል።
ቅርሱ ከድንጋይ፤ ከኖራ፤ ከእንጨት፤ ከጥድ እና ከወይራ የተገነባ መኾኑን ያስታወሱት አሥተዳዳሪው እነዚህን ግብዓቶች በመጠቀም የቅርስ ጥገናው መከናወኑን አብራርተዋል።
ዘላቂነት እና ጥራቱን ለማስጠበቅ በትኩረት መሠራቱንም ገልጸዋል። ጥገናውም የዓለም አቀፍ ቅርስ ሕግን በመጠበቅ የተከናወነ መኾኑን ጠቁመዋል። በቅርስ ጥገናው ላይ ለዘመናት የቆየው የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን ነው የተናገሩት።
በቅርሱ ላይ ምንም አይነት ለውጥ አለመደረጉን ያነሱት አሥተዳዳሪው የኖራው ነጣ ማለት ዘላቂ አለመኾኑን እና በጊዜ ሂደት ወደ ቀደመ መልኩ እንደሚመለስም አብራርተዋል። ጥገናው የቀድሞ ይዘቱን ጠብቆ እንደተሠራም ገልጸዋል።
“ይህ የቅርስ ጥገና የጎንደርን የብርሃን ዘመን የመለሰ መኾኑን” ነው የተናገሩት።
ከቅርሱ ጥገና በፊት ጎብኝዎች ከአንድ ቀን በላይ እንደማይቆዩ ያስታወሱት አሥተዳዳሪው ጥገና መደረጉ እና የግቢው ውበት መጠበቁ የጎብኝዎች ቆይታ እንዲራዘም ዕድል የፈጠረ መኾኑን ተናግረዋል።
የቅርስ ጥገናው በራስ አቅም መሥራት እንደሚቻል የታየበት እና ተሞክሮ የተገኘበት መኾኑንም ጠቁመዋል።
ጎብኝዎች አብያተ መንግሥታቱን 24 ሰዓታት መጎብኘት እንዲችሉ የሚያስችል ተግባር መከናወኑንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
