አምስተኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ በአርባ ምንጭ ከተማ ይካሄዳል።

5

አዲስ አበባ: ሕዳር 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አምስተኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስን አስመልክቶ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ አምስተኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንረንስ ከሕዳር 3 እስከ 4/2018 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ ይካሄዳል ብለዋል።

ኮንፈረንሱ ከዚህ ቀደም በድሬዳዋ፣ በባሕር ዳር፣ በጅማ እና በሀረሪ ከተሞች መካሄዱን የገለጹት ቀሲስ ታጋይ ታደለ ኮንፈረንሱ ሰላምን በመገንባት እና አብሮነትን ለማጽናት ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መኾኑንም ገልጸዋል።

ኮንፈረንሱ እንደ ሀገር ግጭቶችን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ፣ አለመግባባቶችን በውይይት ብቻ እንዲፈቱ ለማስቻል፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ብሎም ኅብረተሰቡን ይበልጥ በማቀራረብ ሰላሙን እንዲጠብቅ ማስቻልን ዋና ዓላማ አድርጎ መዘጋጀቱንም አብራርተዋል።

እስካሁን ተካሂደው ከነበሩት አራት ኮንፈረንሶች ለአንድ ዓላማ በቅንጅት የመሥራት እና ለሰላሙ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ በማድረግ እረገድ ውጤት የተመዘገበበት እንደነበርም አንስተዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው አምስተኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስም ሰላም እና አብሮነት ላይ የሚያተኩሩ የፓናል ውይይቶችን ጨምሮ ከሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል የተውጣጡ ከ40 ሺህ በላይ ተሳታፊ ይኖራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም በመግለጫው ተጠቁሟል።

ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመሬት አሥተዳደር ፖሊሲን ተወዳዳሪ እና ዕውቀት መር ለማድረግ ትብብር አስፈላጊ ነው።
Next articleወጣቶች በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ውጤታማ እንዲኾኑ እየተሠራ ነው።