የመሬት አሥተዳደር ፖሊሲን ተወዳዳሪ እና ዕውቀት መር ለማድረግ ትብብር አስፈላጊ ነው።

2

አዲስ አበባ: ሕዳር 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ የመሬት አሥተዳደር ፖሊሲ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።

ኮንፈረንሱ “የመሬት አሥተዳደር ፍትሕ እና ካሳ ለአፍሪካውያን እና ትውልደ አፍሪካውያን ለኾኑ” በሚል መሪ መልዕክት እየተካሄደ ነው።

“በአፍሪካ ዘላቂ የመሬት አሥተዳደር አቅም ግንባታ ውስጥ የዩኒቨርሲቲዎች ሚና” በሚል ርዕስም የዋናው ኮንፈረንስ አካል የኾነ ምክከር እየተካሄደ ይገኛል።

የአፍሪካ የመሬት አሥተዳደር ዝመና ኔትወርክ 40 ሀገራት፣ 70 የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች እና የምርምር ተቋማት አባል የኾኑበት ነው ተብሏል። በዚህ ኮንፈረንስ ከ18 የአፍሪካ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተገኝተው እየተሳተፉ ነው።

የአፍሪካ ኅብርት ኮሚሽንን የወከሉት ጃኔት ኢዴሜ (ዶ.ር) በትምህርት ተቋማት እና በመንግሥት መካከል ያለውን የግንኙነት ችግር መፍታት በዘርፉ ዕውቀት መር አሥተዳደር በአሕጉሪቱ እንዲኖር ለማድረግ ጠቃሚ ነው ብለዋል።

ይህ ልዩ ኮንፈረንስም ጥልቅ የፖሊሲ መረዳት በመሬት አሥተዳደርም እንዲኖር ለማድረግ አስፈላጊ እንደኾነ አንስተዋል።

በመሬት አሥተዳደር ላይ አዲስ አሠራር ለመተግበር የሚያስችል ተግባራዊ የትብብር መርህ እና አቅጣጫ በዩኒቨርሲቲዎች እና በመንግሥት መካከል እንዲኖር የፖሊሲ እና የዕውቀት እገዛ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኩል መደረግ ይገባዋል ነው ያሉት።

በአፍሪካ በመሬት አሥተዳደር ላይ ተወዳዳሪ የኾነ ፖሊሲ ለማውጣት ተቋማዊ የአሥተዳደር መርህ በአህጉሪቱ እንዲኖር ማድረግ ተገቢ እንደኾነም አንስተዋል።

የጅ አይዜድ ተወካይ ናኒ ዌቸርት በመሬት አሥተዳደር ላይ አዲስ አሠራር ለመተግበር የሚያስችል ተግባራዊ የትብብር መርህ እና አቅጣጫ በዩኒቨርሲቲዎች እና በመንግሥት መካከል እንዲኖር ማድረግ የዘርፉን ትብብር እና ሥራ አንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የጀርመን መንግሥት ሀገራዊ እና አሕጉራዊ ጠንካራ የግንኙነት መስመር ለመዘርጋት እና ለአፍሪካ መሪ የመሬት አሥተዳደር ፖሊሲ እገዛ ያደርጋል ብለዋል። በዚህም አጀንዳ 2063 እንዲሳካ ጂአይዜድ ትብብር እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

የትምህርት ተቋማቱ ከትምህርት ካሪኩለማቸው ቀረፃ እና ማበልፀግ ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

ይህ ምክክርም በፖሊሲ አውጭዎች እና በዘርፉ እጥኝዎች መካከል ያለውን ችግር በመቅረፍ ድልይ ለመኾን እንደሚያገለግል ጠቁመዋል።

በደቡብ አፍሪካ የመንግሥት መሬት አሥተዳደር ከፍተኛ አማካሪ ፕሮፌሰር ግሉንጉዌ ማየንዴ ይህ ውይይት የአፍሪካ የመሬት አሥተዳደር ፖሊሲ አካታች ዕውቀት መር እና ወደፊት ሊኖር የሚችል ችግርን የሚፈታ እንዲኾን ያግዛል ብለዋል።

ያልተገባ ቢሮክራሲ በአፍሪካ የትምህርት ተቋማት እና መንግሥታት ውስጥ የተግባቦት እንቅፋት እየፈጠረ እንደኾነም አስገንዝበዋል።

መፍትሄ አመላካች እና ችግር ፈች ምርምር መሥራት ተቋማቱ ዋነኛ ኀላፊነታቸው ሊኾን ይገባልም ብለዋል። ዩኒቨርሲቲዎች ብቁ ባለሙያዎችን ለሀገራቸው ማብቃት ይገባቸዋል ያሉት ፕሮፌሰር ግሉንጉዌ የመንግሥት እና የተቋማት ፎረም በመመሥረት የሁለቱን አካላት ግንኙነት ቋሚ ማድረግ አንደሚገባም ጠቁመዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገንቢ ትችት በመንግሥታት ላይ ፖሊሲ እስከማስቀየር የዘለቀ የገንቢነት ሚና መጫዎት እንደሚገባውም አብራርተዋል።

ዩኒቨርስቲዎች ለሕግ አውጭወች በቂ የኾነ የፖሊሲ ረቂቅ ማቅረብ ሌላው ትኩረት ሊያደርጉበት የሚገባ ጉዳይ ስለመኾኑም አመላክተዋል።

መንግሥታት ደግሞ ለትምሀርት ዘርፉ እና ተመራማሪዎች የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ እና የሚመጡ የመፍትሄ ሃሳቦችን በቅን እሳቤ መቀበል እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።

በመሬት ካሳ እና ፍትሐዊ አሥተዳደር ላይ መንግሥታት ሊኖራቸው የሚገባ ፖሊሲ ላይ በጋራ መሥራት ለአፍሪካውያን እና ለትውልደ አፍሪካውያን እንደሚጠቅምም አስገንዝበዋል።

በውይይቱ በተለይ በመሬት አሥተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ያሉ የፖሊሲ፣ የምርምር፣ የሕግ እና የካሳ ፖለቲካዊ ዕይታዎች ዙሪያ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በተውጣጡ የትምህርት ተቋማት ተመራማሪዎች፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅት ኀላፊዎች እና በተወካይ ተመራማሪዎች ውይይት እየተደረገ ነው።

ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጤና ሚኒስቴር ጤንነቴ የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያን ይፋ አደረገ።
Next articleአምስተኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ በአርባ ምንጭ ከተማ ይካሄዳል።