አብያተ መንግሥታቱ የተጠገኑት ነባር ይዘታቸውን በጠበቀ መልኩ ነው።

1

ባሕር ዳር: ኅዳር: 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎የጎንደር አብያተ መንግሥታት ከ400 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ ጥንታዊ ቅርሶች ናቸው።

‎ቅርሶቹ በአሠራር ጥበባቸው ፣ በተሠሩበት ቁስ፣ በታሪክ ተናጋሪነታቸው፣ ባስቆጠሩት ዕድሜ እና በሌሎች ጉዳዮች ውብ ናቸው። በዚህም በ1971 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የባሕል እና የሳይንስ ድርጅት (ዩኔስኮ) ዓለም አቀፍ ቅርስ ኾነው ተመዝግበዋል።

‎አብያተ መንግሥታቱ በዕድሜ ብዛት እና በተለያዩ ምክንያቶች ለጉዳት ተጋልጠው ቆይተዋል። አሁን ላይ ግን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ‎አማካኝነት ችግራቸው ተጠንቶ ጥገና ተደርጎላቸዋል።

‎‌የቅርስ ጥገና ጥንታዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ቅርሱን ወደ ነበረበት መመለስ ነው ያሉት የጎንደር ዓለም አቀፍ ቅርስ አሥተዳደር አሥተዳዳሪ ጌታሁን ስዩም ናቸው፡፡

‎የጎንደር አብያተ መንግሥታት ቅርስ ጥገና ጥናቱ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ሢሠራ መቆየቱን ተናግረዋል። ‌በ2016 ዓ.ም ሐምሌ ወር ላይ ደግሞ የጥገና ሥራው ተጀምሮ አሁን ላይ ተጠናቅቆ ለጉብኝት ክፍት ኾኗል ብለዋል።

‎‌ቅርሶቹ የተጠገኑት ነባር ይዘታቸውን በጠበቀ መልኩ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሕጎችን መሠረት ተደርጎ እንደኾነ ገልጸዋል።

‎‌አብያተ መንግሥታቱ የተሠሩበት ቁስ፣ የአሠራር ጥበብ፣ የሠሩት አካላት፣ ዕድሜያቸው እና ሌሎች ሁኔታዎች ለሌላው ዓለም አስተማሪ፣ የሚጠቅሙ ዓለም አቀፋዊ እና ሁለንተናዊ ዋጋ ያላቸው መኾናቸውን ተናግረዋል። ‌አሁን የተደረገው ጥገናም ይህንን መሠረት ያደረገ መኾኑን ነው የገለጹት።

‎‌ወደ ጥገናው ሲገባ ቅርሶቹ የተሠሩባቸው ዋና ዋና ግብዓቶች ድንጋይ፣ ኖራ እና ሀገር በቀል የእንጨት አይነቶችን በመለየት እና የሚገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት ነው ብለዋል።
‎‌
‎በተፈጥሮ ተቆፍሮ የሚወጣ እና በመዶሻ ያልተስተካከለ ድንጋይ፣ በባሕላዊ መንገድ የተቃጠለ ተፈጥሯዊ ኖራ
፤ ለረጅም ጊዜ ተቀብሮ የተዘጋጀ እና ሀገር በቀል ጥቁር እንጨት፣ የሀበሻ ጽድ፣ ወይራ እና ዋንዛ ጥቅም ላይ የዋሉ መሠረታዊ ግብዓቶች እንደኾኑም ተናግረዋል።

“‎‌ጥገናው የተከናወነው ሀገር በቀል ዕውቀት ባላቸው እና ሳይንሳዊ ትምህርት አግኝተው ከ20 ዓመት በላይ ልምድ ባካበቱ ባለሙያዎች” መኾኑንም አንስተዋል።

‎‌ ጥገናውን ቀለል አድርጎ ማየት፣ በአመለካከት በኢትዮጵያውያን አይሠራም ብሎ የማሰብ እና ግብዓቶቹን በቅርብ አለመገኘት በጥገናው ሂደት የነበሩ ችግሮች ናቸው ብለዋል። ችግሮችን በመጋፈጥ በሚፈለገው መንገድ እና ደረጃ ጥገናው መሳካቱን ተናግረዋል።

‎‌በጎንደር አብያተ መንግሥታት በተለያዩ ጊዜያት ጉዳት በደረሰባቸው ላይ የሚደረጉ ጥገናዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

‎አሁን የተደረገለት ጥገና ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ጥንታዊ ይዘቱን ጠብቆ መጠገኑ፣ ሁሉንም ቅርሶች በአንድ ጊዜ መጠገኑ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ መጠናቀቁ እስካሁን ሲደረጉ ከነበሩ ጥገናዎች የተለየ ያደርገዋል ነው ያሉት።
የቆዩት ጥገናዎች እንዲቆይ ለማስቻል እንጅ በቅርሱ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት አልቻሉም ነበር ነው ያሉት።

ሁሉም ቅርሶች ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች መጠገናቸውንም አንስተዋል።

‎‌ከዚህ በፊት አብዛኞቹ የቅርሱ ክፍሎች በደረሰባቸው ጉዳት ለደኅንነታቸው ሲባል ታች መሬት ላይ ኾኖ መመልከት እንጅ ውስጥ ገብቶ መጎብኘት የማይቻሉ ነበሩ ነው ያሉት። አሁን ላይ በመጠገናቸው ከ50 በላይ ክፍሎችን ውስጥ ገብቶ መጎበኘት አስችሏል ብለዋል።

‎‌ከጥገናው በተጨማሪ ሕንጻዎቹ በፊት ይሰጡት የነበረውን አገልግሎት ማስጀመር እንደታሰበም አንስተዋል። ይህም በቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ነው ያሉት።

‎ለአብነትም የመዝገብ ቤት ክፍሉ በፊት ዜና መዋዕል ሲጻፍበት የነበረውን የብራና ሥራ በአውደ ርዕይ ማሳየት ይጀመራል ብለዋል።

‎ይህ መኾኑ ቱሪስቶች በከተማው ያሳልፉት የነበረውን ጊዜ በመጨመር የቱሪዝም ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦውን ከፍ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡

‎የሕዝብ ጥያቄ የነበረው የአንበሳ ቤት በተገቢው መንገድ አናብስትን ለማስገባት ታሳቢ ተደርጎ ተጠግኗልም ብለዋል፡፡

‎ለቱሪስቶች ምቹ ተደርጎ ለ24 ሰዓታት የጉብኝት አገልግሎት እንዲሰጥ በሚያመች መልኩ ተሠርቷል ነው ያሉት፡፡ የቤተ መንግሥት ሕይዎትን የሚያሳዩ አውደ ርዕዮች እንደሚኖሩም ጠቁመዋል፡፡

‎የጎንደር ዓለም አቀፍ ቅርስ አሥተዳደር የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እና የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል በሚፈለገው ደረጃ እንዲኾን መዋቅር እየተሠራለት መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleወጣቶች በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ውጤታማ እንዲኾኑ እየተሠራ ነው።
Next articleየጤና ሚኒስቴር ጤንነቴ የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያን ይፋ አደረገ።