
ፍኖተ ሰላም: ኅዳር 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ግሎባል ኢንተርፕርነር ሽፕ ዊክ ከኢንተርፕርነር ዲቨሎፕመንት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በፍኖተ ዳሞት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ለጀማሪ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች የሥራ ፈጠራ ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
የፍኖተ ዳሞት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አንተነህ ባሕሩ ሥልጠናው ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች አዳዲስ ሃሳቦችን እንዲያመነጩ እና እንዲያንሸራሸሩ ዓላማ ያደረገ መኾኑን ተናግረዋል።
ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች በሥልጠናው በሚያገኙት ግብዓት የንግድ ሥራቸውን እንዲያሳድጉ እና እንዲያስፋፉ ዓላማ ያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ሥራ እና ክህሎት መምሪያ ምክትል ኀላፊ አያልሰው ሙሉ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲኾኑ እና በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ውጤታማ እንዲኾኑ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ሥራ ፈጣሪዎች አቅማቸውን እንዲያሻሽሉ በማድረግ የብድር እና የሥራ ማስፋፊያ ቦታ በማመቻቸት ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱንም አስረድተዋል።
ከሥራ ፈጣራ ባሻገር የፋይናንስ አያያዝ እና አጠቃቀማቸውን እንዲያጎለብቱም ታስቦ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሥራ ፈጠራ ሥልጠናው በዞኑ በሌሎች አካባቢዎችም ተጠናክሮ እንደሚሰጥ አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
