
አዲስ አበባ: ኅዳር 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ልማራዊ ሴፍቲኔት እና ሥራ ፕሮጀክት የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን መንግሥት ለሰው ተኮር ልማት ልዩ ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል።
ከሰው ተኮር ልማት ተግባራት መካከል አንዱ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት እና ሥራ ፕሮጀክት መኾኑን ተናግረዋል።
መንግሥት በ2017 በጀት ዓመት ለከተሞች በጀት መድቦ በተደረገዉ ጥረት በርካታ ዜጎችን ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ወደ አምራችነት መቀየራቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት በሰጠችው ልዩ ትኩረት እና ለተመዘገቡ ስኬቶች የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እውቅና መስጠታቸውንም ተናግረዋል።
ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን አንስተዋል። ሦሥተኛ ዙር እንዲቀጥልም 250 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አድርገዋል ነው ያሉት።
የዛሬው መድረክ ከተገኙ ስኬቶች እርስ በርስ የምንማማርበት እና ለቀጣይ ሥራዎች የጋራ አቅጣጫ የምናስቀምጥበት ነው ብለዋል።
የቢሾፍቱ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ዘሃራ ከድር በከተማዋ የነዋሪዎችን ኑሮ የሚያሻሽሉ እና ከተማዋን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርጉ በርካታ ሥራዎች እየተከናዎኑ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በከተማዋ 35 የሆቴል ግንባታዎች፣ 45 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት፣ 51 የአረንጓዴ ፓርኮች እና 28 የመኪና ማቆሚያ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
በከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት እና ሥራ ፕሮጀክት ከ10 ሺህ 242 በላይ ዜጎችን ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ወደ አምራችነት ለመቀየር የተለያዩ ተግባራት እየተከናዎኑ መኾናቸውን አንስተዋል።
እስካሁን 745 ሰዎች ሽግግር አድርገዉ ራሳቸዉን ችለዋል፤ ከ2 ሺህ 542 በላይ የሚኾኑት ደግሞ ለምረቃ ተዘጋጅተዋል ነዉ ያሉት።
የተመዘገቡ ስኬታማ ተሞክሮዎች ልምድ የሚቀርብበት እና የቀጣይ አቅጣጫ የሚቀመጥበት መኾኑም ተመላክቷል።
ዘጋቢ:- ኢብራሂም ሙሃመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
