“ዙፋን የረጋብሽ፣ ሥልጣኔ ያበበብሽ”

4
ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እርሷ ዙፋን ናት ሀገር ከእነክብሯ የተቀመጠችባት፤ እርሷ ዘውድ ናት ሀገር የነገሠችባት፤ እርሷ በትረ መንግሥት ናት ንግሥና የተጨበጠባት፤ እርሷ የንግሥና ቀለበት ናት ለሀገር ቃል ኪዳን የታሠረባት፤ እርሷ ካባ ናት የሀገር ክብር የሚለበስባት።
እርሷ መሰሶ ናት ሀገር የቆመችባት፤ እርሷ ማገር ናት ሀገር የጸናችባት፤ እርሷ ተራራ ናት ታላቅነት የሚለካባት፤ እርሷ መስታውት ናት ትናንት የሚታይባት፤ እርሷ ብራና ናት ገናና ታሪክ የሚነበብባት፤ እርሷ ዥረት ናት ኢትዮጵያዊነት ያለ ማቋረጥ የሚፈስባት፤ እርሷ ውቅያኖስ ናት ታሪክ የሚቀዳባት፤ አንድነት የሚጠጣባት።
እርሷ መዘክር ናት ታሪክ የሚጎበኝባት፤ እርሷ ዋርካ ናት ታላለቆቹ የሚያርፉባት፤ የተጣላን የሚያስታርቁባት፤ እርቅን የሚያጸኑናት፤ ጥልን የሚያጠፉባት፤ እርሷ የፍቅር አዳራሽ ናት ሕዝብ ሁሉ በአንድነት የሚሰባሰብባት፤ ስለ አንድነት የሚመከርባት፤ ስለ ፍቅር የሚዘከርባት።
“ዙፋን ረግቶባታል፤ ሥልጣኔ አብቦባታል”፤ የሀገር ክብር ከተራራ ገዝፎ ታይቶባታል፤ የሀገር የአንድነት ከአለት ጠንክሮባታል፤ የሀገር ሉዓላዊነት ጸንቶባታል፤ ኢትዮጵያዊነት እንደ ማለዳ ጀንበር በርቶባታል፣ ጥበብ ደምቆ ኖሮባታል ጎንደር።
ባለ ግርማ ነገሥታት በክብር ነገሠውባታል፤ የታላቋን ሀገር ታላቅነት ከፍ አድርገውባታል፤ መኳንንቱ እና መሳፍንቱ ለሀገር የሚበጀውን፣ ለሕዝብ የተገባውን መክረውባታል፤ የጦር አበጋዞቹ ስለ ሀገር ሉዓላዊነት፣ ስለ ከበረች ነጻነት በአንድነት ተሰልፈውባታል፤ ትጥቃቸውን አጥብቀው፤ ልባቸውን በወኔ መልተው በኩራት እና በተጠንቀቅ ኖረውበታል፤ ሊቃውንቱ በጥበብ ተራቅቀውባታል፤ ያለ ማቋረጥ ዕውቀትን ዘርተውባታል፤ ያማረውን ዘር እያበቀሉ፤ ፍሬውን አይተውባታል።
ወይዛዝርቱ እንደ ጀንበር አበሩባት፤ ጎበዛዝቱ በክብር ታዩባት፤ ደጋጎቹ ያለ ማቋረጥ ተመላለሱባት፤ በደግነታቸው ጎበኟት፤ መልካሙን ነገርም ሠሩባት።
ጎንደር ምስጢር በበዛባቸው ተራራዎች የተከበበች፤ ራሷም ተራራ የኾነች፤ የታሪክ ተራራ፣ የሥልጣኔ ተራራ፣ የዕውቀት ተራራ፣ የባሕል ተራራ፤ የሃይማኖት ተራራ የገነባች፤ ትናንቷን ያላጣች ከእነ ክብሯ የኖረች ከከተማ ባሻገር የኾነች ውብ ሥፍራ ናት።
አበው ጡብ ደርድረው ከዘመን የቀደሙ አብያተ መንግሥታትን የሠሩባት፤ የአፍሪካን መነጋሻነት ያጸኑባት፤ እጹብ የሚያሰኙ አብያተ ክርስቲያናትን ያነጹባት፤ ባሕል፣ ታሪክ፣ እሴት እና ሃይማኖት ተባብረው የሚኖሩባት፤ አንድነት፣ ጀግንነት፣ ሀገር ወዳድነት፣ ሠንደቅ ዓላማ አፍቃሪነት፣ ደግነት እና እንግዳ ተቀባይነት ሳይነጣጠሉ የሚኖሩባት ጥንታዊት ከተማም ናት።
“እንዲህ ቅርብ ነው ወይ ጎንደር ለፀሐይ
ጎህ ሳይቀድ ማለዳ አብሮቶ የሚታይ” እንዳለች ዘፋኟ ጎንደር ገና የሥልጣኔ ጎህ በማይታይበት ዘመን በሥልጣኔ አብርታ የታየች፣ የሥልጣኔ ጮራ ናት።
ዓለማየሁ ገላጋይ መለያየት ሞት ነው በተሰኘው መጽሐፋቸው ጎንደር ዓመት እንደ ዓለት ቢነባበርባት የማይቀብራት ከተማ ናት፡፡ ሁልጊዜም ከታች ሆኜ ወደ ላይ የማያት ደብር ናት አላት። እንደ ብዙ ከተሞች የማይጮህባት፣ ጥንታዊ አስተዋይነት የረበበባት ናት፡፡ ሁልጊዜም ጎንደር ስሄድ ላለፈው ማንነቴ የአሁን እኔነቴ ይሰግዳል፤ ይገብራል፣ ይጎናበሳል፤ ጎንደር የሕልሜ ከተማ ናት ይሏታል።
ጎንደር ሄዶ የፋሲል ግንብን አይቶ በቅድመ አያቶቹ የማይኮራ ማነው? ጎንደር ወቀሳዬ ናት። እዚያ ሄጄ ስመለስ ቀና ማለት ያቅተኛል፣ መንፈሴ ይጎብጣል፤ ነፍሴ በመጻጉነት ትቃትታለች ነው የሚሏት።
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ መዝገበ ቃላት ሐዲስ በተሰኘው መጽሐፋቸው ጎንደር ጉንደ ሀገር፣ የፋሲል ከተማ፣ ደብር፣ መናገሻ ታላቅ መዲና ብለው ገልጸዋታል። ጎንደር የኢትዮጵያ ብቻ ሳትኾን የአፍሪካ መናገሻ እየተባለች የምትጠራ የገናና ታሪክ ባለቤት ናትና።
አሰግድ ተስፋዬ ደግሞ ጎንደር የአፍሪካ መናገሻ በተሰኘው መጽሐፋቸው ጎንደር ማለት የሀገር መሠረት፣ የሀገር ግንድ፣ ታላቅ ምድር፣ የሀገር ቀንዲል ማለት ነው ብለው ጽፈዋል።
ይህች የሀገር ቀንዲል፣ የሀገር አክሊል፣ አድባር፣ ዋልታና ማገር የኾነች ከተማ በጥንታዊ አብያተ መንግሥታቷ እና በአብያተ ክርስቲያናቷ፣ በበዙት ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ሃብቶቿ በዓለም ፊት ተወዳጅ ኾና ኖራለች።
ታዲያ እነዚህ ጎንደር ሥልጣኔን ያመጠቀችባቸው፤ ኢትዮጵያ በዓለም ፊት የምትገለጽባቸው፤ የዓለምንም ቀልብ የምትስብባቸው የጎንደር አብያተ መንግሥታት ባለፉት ዓመታት በዕድሜ መግፋት ምክንያት ተጎድተው ቆይተዋል።
እኒያ ሥልጣኔ እንደ ጮራ የበራባቸው አብያተ መንግሥታት ተንደው ይፈርሱ፤ ፈርሰው ይጠፉ ይኾን የሚል ስጋትም ነበር። አሳምረው የሠሯቸው፤ የኢትዮጵያን ገናናነት ያተሙባቸው ነገሥታቱ ስማቸውን በወርቅ ቀለም ጽፈው ካለፉ በኋላ የጎንደር አብያተ መንግሥታት አያሌ ፈተናዎችን አሳልፈዋል። የተፈጥሮ እና የሰው ሠራሽ መከራዎች ተፈራርቀውባቸዋል።
ለወትሮው በዙሪያቸው እንደ አንበሳ የጀገኑ፣ እንደ ነብር የፈጠኑ የቤተ መንግሥት ጠባቂዎች፤ ያማረውን ልብስ ለብሰው የሚፋጠኑ የእልፍኝ አስከልካዮች፤ ልብ የሚያርድ ግርማ ያላቸው የጦር አበጋዞች፣ መልካም የሚመክሩ፣ በግርማቸው የሚያስፈሩ መኳንንት እና መሳፍንት፣ በወርቅ ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታት እንዳልነበሩባቸው፣ አያሌ ታሪክ እንዳልተሠራባቸው፤ የኢትዮጵያ ክብር እና ልዕልና ከፍ ከፍ እንዳላለባቸው ተረስተው ኖረዋል፤ አስታዋሽ እስኪያገኙ ድረስ የከበረውን ታሪክ ይዘው ዘመናትን ተሻግረዋል።
ታሪካቸውን የሚያስታውስ ትውልድ እስኪመጣ ድረስ በእርጅና ገፍተዋል። እነኾ ዘመን ደረሰ፤ የአባቶችን ታሪክ የሚያስታውስ፤ የቆዬውን ታሪክ የሚጠብቅ፣ የሚያስጥብቅ፤ ከክብራቸው ሳይጎድሉ ለትውልድ እንዲተላለፉ የሚያደርግ ትውልድ ተገኘ። እርጅና የተጫጫናቸው የጎንደር አብያተ መንግሥታት እንደ ቀደመው ዘመን ሁሉ አማሩ፤ ተዋቡ፤ የእርጅና ዘመናቸው ታደሰ፤ የቀደመ መልካቸው ተመለሰ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሃሳብ አመንጭነት፣ የሥራ አቅጣጫ እና ክትትል የጎንደር አብያተ መንግሥታት ተጠግነው እያበሩ ነው፤ የትናንት ታሪካቸውን እና መልካቸውን እንደጠበቁ በተራራው አናት ላይ በግርማ እየታዩ ነው።
ጎንደርም እያበራች፣ ተሞሽራለች፤ የቀደመ ደም ግባቷን ገልጣለች። ያረጀ የመሰለውን ውበቷን ከተደበቀበት አውጥታለች።
“የሀገር ተምሳሌት ጎንደር አዛውንቷ
ከእነ ሙሉ ክብሯ ከእነ ምልክቷ
ዘመን ሳይጫነው ሳያረጅ ውበቷ
ዛሬም እንዳለ ነው ፍቅር እና እምነቷ” እንዳለች ከያኟ ጎንደር ውበቷ ሳያረጅ፣ ፍቅር እና እምነቷ ሳይቀንስ ዛሬም አለ፤ ነገም ይኖራል። ስለምን ቢሉ የፍቅር እና የእምነት ከተማ ናትና።
” የጎንደር እልፍኝ አቤት ስፋቱ
የተመቸ ነው ቤተ መንግሥቱ” እንዳለች ከያኟ ዳግም ያበራችው ጎንደር በሰፊው እልፍኟ፣ በተመቸው ቤተ መንግሥቷ እንግዶቿን ያለ ማቋረጥ ትቀበላለች፤ ሽርጉድ ብላ ታስተናግዳለች፤ ሞሽራ ታሰነብታለች፤
ትዝታን፣ ፍቅርን እና ታሪክን አስይዛ ትሸኛለች።
ጎንደር ዙፋን የረጋብሽ፤ ሥልጣኔ ያበበብሽ፤ ክብር እና ግርማ የመላብሽ፤ ታሪክና ሃይማኖት የጸናብሽ፤ ባሕል እና እሴት የደረጀብሽ፣ ኢትዮጵያዊነት እና አንድነት የጠነከረብሽ፤ የሀገር ፍቅር እንደ ሚነድ እሳት የሚንቀለቀልብሽ የአፍሪካ መናገሻ ነሽ።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“አሚኮ የብሔረሰቦች ባሕል እና ቋንቋ እንዲያድግ ሠርቷል፤ እየሠራም ነው” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ
Next articleየደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ጥሩ አፈጻጸም ላሳዩ የፖሊስ እና የአድማ መከላከል አባላት የማበረታቻ ሽልማት እና ዕውቅና ሰጠ።