መንገድ ላይ መሽናት ለምን?

2
ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እዚህ አከባቢ መሽናት 200 ብር ያስቀጣል ይላል!” ይላል። ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ዓባይ ማዶ በሚባለው የከተማው ክፍል ዋናው አስፋልት ዳር ያየኹት ማስታወቂያ ነው፡፡
ማስታወቂያውን እና በማስታወቂያው ሥር ያለውን እውነት ስመለከት ሳቄን መቆጣጠር አልቻልኩም፡፡
ማስታወቂያው በዚያ አከባቢ መሽናት 200 ብር እንደሚያስቀጣ ቢናገርም ከማስታወቂያው ሥር ያለው የሽንት ብዛት እና መጥፎ ጠረን ግን እዚያ ጋር መሽናት ያሸልማል እንጂ ያስቀጣል የሚል አይመስልም፡፡
ቦታው የከተማ አውቶብሶች እና ታክሲዎች የሚቆሙበት በመኾኑ ተሳፋሪዎች ያንን የሽንት ብዛት ወደ አፍንጫቸው መሳባቸው የግድ ነው፡፡ የኔ ትዝብት “መሽናት ክልክል ነው” ማለት ከመቼ ወዲህ “መሽናት ልክ ነው” በሚል እንደተተረጎመ አለማወቄ ነው፡፡
ውቧ ባሕር ዳር እያልን የምናሽሞነሙናት ከተማችን በእርግጥም ውበቷ የማይካድ ቢኾንም ውበቷን የሚያጠለሹ በርካታ ተግባራት እንደሚፈጸሙባትም መካድ የለብንም፡፡ በነገራችን ላይ የትዝብቴ መነሻ እዚሁ ባሕር ዳር ከተማ ላይ ኾነ እንጅ ሁሉም ከተሞቻችን የዚሁ ተግባር ተጋላጮች ናቸው።
ከላይ ለአብነት ብዬ ያነሳሁት የዓባይ ማዶው የንጽሕና ጉድለት ለከተማ አሥተዳደሩ ዓይኖች የራቀ ነው ብንል እንኳን ይኼኛው ትዝብቴ ደግሞ ይበልጥ የሚያስተዛዝበን ጉዳይ ኾኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 04 ከከተማ አሥተዳደሩ ወደ ዓለም አቀፉ የባሕር ዳር ስታዲየም በሚወስደው የጌጠኛ መንገድ (ኮብል ስቶን) ላይ ከከተማ አሥተዳደሩ በቅርብ ርቀት ላይ በየአጥሩ ሥር ሽንት እና ከሽንት የከፋውን የሰዎች ጽዳጅ ማየት በእጅጉ ያስደነግጣል፡፡ በውበቷ ላይ ውበት እየደረበች በመፍካት ላይ ለምትገኘው ከተማም የማይመጥን እንከን ነው።
ባሕር ዳርን ለማስዋብ ማልደው አስፋልቱን የሚያጸዱ እና አትክልቶቹን ውኃ የሚያጠጡ በርካታ የከተማ አሥተዳደሩ የከተማ ውበት ሠራተኞች እንዳሉ መካድ አይቻልም፡፡ ችግሩ የከተማዋ ውበት ታጥቦ ጭቃ እንዲኾን የሚያደርጉ ከጽዳት ሠራተኞቹ በእጥፍ የሚበልጡ አጥፊዎች መኖራቸው ላይ ነው፡፡
ከከተማ አሥተዳደሩ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው የመስቀል አደባባይ ሜዳ አጥር ሥር ሰዎች ጨለማን ተገን አድርገው የተጸዳዷቸውን ቆሻሻዎች በጠራራ ጸሐይ አፍንጫችንን ይዘን እንድንሄድ ከማስገደዳቸው የበለጠ የሚያስተዛዝበን ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡
ትዝብቴ የከተማ አሥተዳደሩ ለባሕር ዳር ከተማ ውበት የሚያደርጋቸውን ጥረቶች አሳንሶ ማየት አይደለም። ይልቁንም እንደ አንድ የከተማዋ ነዋሪ ባሕር ዳርን ከውበት ማማዋ በሚያወርዷት አጥፊዎች ላይ የጋራ የኾኑ ሥራዎች መሠራት አለባቸው ማለት ፈልጌ እንጂ፡፡
በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የሚያድሩ ተሳቢ መኪናዎች ጎማ ሥር ሽንት መሽናትም የተፈቀደ ያህል ኾኖ አይቼዋለሁ፡፡ እነዚህ ተሳቢዎች የሚጭኑትን ጭነው ወይም ጉዳያቸውን ጨርሰው ከቆሙበት አከባቢ ሲንቀሳቀሱ ያ አከባቢ በሽንት፣ በግራሶ፣ በተቃጠለ ዘይት እና በሌሎችም ቆሻሻዎች ተጥለቅልቆ ማየትም በእጅጉ ያሳዝናል፡፡
ዓባይ ማዶ ያየሁትን አንድ ሌላ ማስታወቂያም ልጨምርላችሁ፡፡ “እዚህ አከባቢ መሽናት በቤተ ክርስቲያኗ ስም የተወገዘ ነው” ይላል፡፡ መሽናት ክልክል ነው፣ መሽናት ብር ያስቀጣል እና በሌሎችም ማስታወቂያዎች አልመለስ ያለውን ሰው በቤተ እምነት እስከማስፈራራት መደረሱ እኛ ሰዎች ምን ያህል ግብዝ ብንኾን ነው አያስብልም ትላላችሁ?
ይህ ትዝብቴ ታዝቦ ማለፍ ብቻ እንዳይኾንብኝ መፍትሔ ይኾናል ያልኩትንም ሃሳብ ላዋጣ፡፡ የከተማ አሥተዳደሩ በጎዳናዎች ላይ እያደሩ በየ አጥሩ ጥግ የሚጸዳዱትን ዜጎች የመጸዳጃ ቦታ (በነጻ) ቢያመቻችላቸው ጥሩ ይመስለኛል፡፡ በነጻ ያልኩት ለመጸዳዳት ገንዘብ የሚያወጡ ከኾነ ገንዘብ ላለማውጣት ሲሉ ጨለማን ተገን አድርገው መጸዳዳትን ምርጫቸው ያደርጋሉ ብዬ ነው፡፡
በከተማዋ ውስጥ የተበራከቱት የድራፍት እና ሌሎች መጠጥ ቤቶች ለሚያጠጧቸው ደንበኞች በቂ የኾነ መጸዳጃ ቦታ ስለማያዘጋጁ ጠጪዎቹ ከመጠጥ ቤቶቹ እየወጡ በየ አጥሩ ጥግ ይሸናሉ፡፡ ይሄው ዶፍ የሽንት ዝናብ ደግሞ የከተማዋን መዓዛ ሽንት ሽንት እንዲሸት ያደርገዋልና የከተማ አሥተዳደሩ በዚህም ዙሪያ ጠንካራ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅበታል፡፡
በመጨረሻም ባሕር ዳር በኮሪደር ልማት እየተዋበች ቢኾንም እነዚሁ ለውበት ቦታ የማይሰጡ ሰዎች በአስፋልት ዳር እና በድንጋይ ንጣፍ መንገዱ ላይ የለመዱትን ወደ ኮሪደሩ አያመጡትም ብሎ ማሰቡ የዋህነት ነው፡፡
መፍትሔው መጸዳዳት ክልክል በኾኑባቸው ቦታዎች ሁሉ መጸዳዳት ክልክል መኾኑን በተግባር ማረጋገጥ ነው፡፡ ካልኾነ ግን መጸዳዳት ክልክል በኾነባቸው ቦታዎች ሁሉ መጸዳዳት ልክ ኾኖ የሚቀጥል ይኾናል እንደማለት ነው፡፡
በእሱባለው ይርጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ምን ይልህ ሸዋ”
Next articleንጹሐን በግፍ የተሰውበት ቀን በማይካድራ እየታሰበ ነው።