
ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ከአባታቸው ከሸዋው ንጉሥ ኃይለ መለኮት ሣህለ ሥላሴ እና ከእናታቸው ወይዘሮ እጅጋየሁ ለማ አድያም ነሐሴ 12/1836 ዓ.ም በደብረ ብርሃን አካባቢ አንጎለላ በሚባል ሥፍራ ነው የተወለዱት፡፡
አያታቸው ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ የልጁን መወለድ ሲሰሙ “ምን ይልህ ሸዋ” በሉት ብለው ስም አወጡ።
ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ “ምኒልክ በሚል ስም የሚነግሥ ንጉሥ ኢትዮጵያን ታላቅ ያደርጋታል” የሚል ትንቢት ስለነበር “ምኒልክ” የኔ ስም ነው ብለው ነበር።
ኾኖም በህልማቸው ከልጁ ጋር አብረው ቆመው ከሳቸው ጥላ የልጁ ጥላ በልጦ፤ በእግር የረገጡትን መሬት ሲያለካኩ እሳቸው ከረገጡት ልጁ የረገጠው ረጅም ኾኖ አዩ።
ከዚህ በኋላ “ምኒልክ የኔ ስም አይደለም፤ የሱ ነው። ስሙን ምኒልክ በሉት” ብለው አዘዙ ይላሉ ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” በተባለው መጽሐፋቸው። ምኒልክ ብዙ ውጣ ውረዶች አልፈው የሸዋ ንጉሥ መኾንም ችለዋል፡፡
በወቅቱ ንጉሥ ምኒልክ አጼ ዮሐንስ ወደ መተማ ሲዘምቱ ምናልባት ክፍተት እንዳይኖር እና ድርቡሽ ሕዝብን እንዳይጎዳ በሚል በወሎ እና በበጌ ምድር ወሰን ኾነው ለመጠባበቅ ሲሉ ቀወት የሚባል ሥፍራ ሲደርሱ የንጉሠ ነገሥቱን መሞትን አረዷቸው። የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ ለአራት ቀናትም በሀዘን ሰነበቱ።
ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” በተባለው መጽሐፋቸው የንግሥናውን ሥርዓት እንደተነተኑት ከሀዘን መልስ የንግሥና በዓሉ ሥርዓት እየተዘጋጀ ከርመው ጥቅምት 25/1882 ዓ.ም በዚህ ሳምንት የሸዋ ንጉሥ የነበሩት ንጉሥ ምኒልክ ኃይለመለኮት ሣህለ ሥላሴ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ በእንጦጦ ርእሰ አድባራት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በተፈጸመው ሥርዓት ንጉሠ ነገሥት ኾኑ።
በሰዓቱም በጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ እጅ የወርቅ ሰይፍ ታጥቀው፤ በወርቅ ሽቦ የታሸጉ ሁለት ጦሮች ጨብጠው፤ የወርቅ ዘንግ ከተሰጣቸው በኋላ ቅብዐ መንግሥቱን ተቀብተው፣ “ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ፤ ዳግማዊ ምኒልክ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” ተብለው የወርቅ ዘውድ ተደፋላቸው።
የቅዳሴውም ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ አጼ ምኒልክ በውጭ ሀገር በአምስት ሺህ ብር የተሠራ ካባቸውን ለብሰው፣ ባለወርቅ ጥላ ተይዞላቸው ዘውዳቸውን ደፍተው የወርቅ ዘንግ ይዘው የወርቅ ጫማ አድርገው ካህናቱ ከፊት እና ከኋላ እያጠኑ በራሶች እና ደጃዝማቾች ታጅበው ከቤተ ክርስቲያኑ ብቅ አሉ።
እጅግ በጣም በዝቶ የተሠበሠበው ሕዝብም የዘንባባ ዝንጣፊ እየያዘ “ሺህ ዓመት ያንግሥዎ” እያለ ደስታውን በእልልታ እና በሁካታ ገለጠ።
ከቤተ መንግሥታቸው ውስጥ ከተዘጋጀው የግብር ማብያ ዳስ ገብተው ከተዘጋጀላቸው ዙፋን ላይ ሲቀመጡ 101 ጊዜ መድፍ ተተኮሰ።
ከመድፎቹ መተኮስ ጋርም ጠቅላላው ሠራዊት የያዘውን ጠመንጃ በተኮሰ ጊዜ የጭሱ ብዛት እንደ ደመና ኾነ” ብለው አስፍረዋል።
ንጉሡ “አጼ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” የሚለውን ስም በተቀዳጁ በማግሥቱ ጥቅምት 27/1882 ዓ.ም በዚህ ሳምንት ጣይቱ ብጡል እቴጌ ተብለው ተሰይመዋል።
የሥርዓተ ዘውዱ አፈጻጸም በከፍተኛ መሰናዶ የተጠናቀቀ በመኾኑ እጅግ ደማቅ እንደነበር ከተጻፉ ጹሑፎች ለማወቅ ይቻላል።
እቴጌ ጣይቱም ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ ከንጉሠ ነገሥቱ እጅ የተቀበሉትን ዘውድ ደፉላቸው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በታወቁበት “እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ” በሚል የክብር ስም ማኅተም ተቀረጸላቸው።
የአጼ ምኒልክ ባለቤት የእቴጌ ጣይቱ ሆቴል በኢትዮጵያ ቀዳሚው ሆቴል መኾኑን በርካታ ድርሳናት መዝግበዋል፡፡ ሆቴሉ በ1898 ዓ.ም በነሐሴ ወር ግንባታው ተጀምሮ በ1900 ዓ.ም ጥቅምት 25 በዚህ ሳምንት ተመርቆ መከፈቱን ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” በተሰኘው እና የአጼ ምኒልክን ታሪክ እና ተግባራት በከተቡበት መጽሐፍ ይገልጻሉ፡፡
በዘመኑ በነበረው ባሕል እና ማኅበረሰባዊ አስተሳሰቦች ምክንያት በወቅቱ ሆቴል ከፍቶ “ምግብ ከፍላችሁ ተመገቡ፤ መጠጥም እንዲሁ” ማለት አስቸጋሪ ነበር፡፡
ሆቴሉ እንኳን ቢገኝ ከፍሎ መመገብ እንደነውር የሚታይ በመኾኑ ሕዝቡም ኾነ መኳንንቱ ስለማይፈጽሙት ጉዳዩ ንጉሡን አጼ ምኒልክንም ኾነ እቴጌ ጣይቱን እጅጉን አሳስቧቸው ነበር፡፡
እናም ምኒልክ እና ጣይቱ ይህንን መፈጸም ነውር እንዳልኾነ በቅርባቸው ላሉ መኳንንት ከማስረዳት ባለፈ በርካታ ጥረቶችን አድርገዋል፡፡ ነባሩን ባሕል እና ልማድ በጠበቀ ማኅበረሰብ ውስጥ አዲስ ባሕልን መትከል ቀላል አይደለምና፡፡
እንደ ጳውሎስ ኞኞ መረጃ “ጣይቱ እጅ የሚያስቆረጥም ወጥ እያሠሩ ገበያ ቢጠብቁ ጠፋ፤ ጣይቱ ጠዋት የሚያሠሩት ወጥ ለሠራተኞቹ የማታ ራት ይኾን ጀመር፡፡
የባለቤታቸው ገበያ ማጣት ያሳሰባቸው አጼ ምኒልክ አንድ ቀን ከችሎት ሊነሱ ሲሉ በአካባቢያቸው ላሉ መኳንንቶች “ጣይቱ ምግብ የሚሸጥበት ቤት ከፍታለችና ኑ እንሂድና ልጋብዛችሁ” ብለው ወሰዱዋቸው፡፡
መኳንንቱ በሉ ጠጡና ንጉሡ ምኒልክ 30 ብር ከፈሉ፡፡ በማግሥቱ እንደተለመደው ገበያ ቢጠበቅ ጠፋ፡፡
እንደገና አጼ ምኒልክ ሆቴል ገብቶ መብላት ነውር ያለመኾኑን ለመኳንንቱ ገልጸው እንደገና ምሳ ጋበዙ፡፡ በሌላው ቀን አሁንም ገበያ አልተገኘም፡፡ ቢጠበቅ ቢጠበቅ ድርሽ የሚል ሰው ጠፋ፡፡
በሌላ ቀን ደግሞ አጼ ምኒልክ ከችሎት ሊነሱ ሲሉ በዙሪያቸው ላሉ መኳንንት “ሰማችሁ ወዳጆቼ” አሉ:: “በፈረንጅ ሀገር አንድ ቀን አንድ ሰው የጋበዘ እንደኾነ ያ የተጋበዘ ሰው በሌላ ቀን ደግሞ ብድሩን ይከፍላል ብድሩን ካልከፈለ ግን እንደ ነውር ይቆጠርበታል” ብለው ንግግራቸውን ሳይጨርሱ መኳንንቱ “እርስዎን ፈርተን እና አፍረን ነው እንጂ የሚሆንልን ከኾነ የአጼ ምኒልክን ብድር ለመመለስ እኔ አለሁ” እያለ ተራ በተራ ከሆቴል ቤት ምኒልክን እና ጣይቱን ይጋብዝ ጀመረ፡፡
ገበያ እየደራ ሄደ፡፡ ምሳችንን እቴጌ ሆቴል ሄደን እንብላ የሚለው ስለበዛም ስሙ እቴጌ ሆቴል ተባለ፡፡
በእግር ኳሱ ዓለም ውጤታማ የሚባሉት አሠልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ታላቁን ክለብ ታላቅ ለማድረግ ማንችስተር ዩናይትድን የተረከቡት ጥቅምት 27/1986 ዓ.ም በዚሁ ሳምንት ነበር።
የማንቸስተር ዩናይትድ ብቻ ሳይኾን ከእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የምንጊዜም ምርጥ አሠልጣኞች ውስጥ የፊት መሥመሩን የሚይዙ ውጤታማ አሠልጣኝም ናቸው አሠልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን፡፡
በክለቡ በቆዩባቸው 27 ዓመታት ከሀገር ውስጥ ውድድር ጀምሮ እስከ አውሮፓ እና ዓለም አቀፍ ክብሮችን አግኝተዋል፡፡
እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን በ1986 ማንቸስተር ዩናይትድን የተረከቡት ስኮትላንዳዊው ሰው ለ19 ዓመታት ከዋንጫ ጋር የተለያየውን ክለብ ወደ ስኬት በመመለስ ስማቸውን ከክለቡ ጋር አያይዘዋል።
የ83 ዓመቱ አሠልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በክለቡ በቆዩባቸው 27 ዓመታት 13 የፕሪሚየር ሊግ እና ሁለት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 38 ዋንጫዎችን ማሳካት ችለዋል።
አሠልጣኙ በማንችስተር ዩናይትድ ቤት 1ሺህ 500 ጨዋታዎችን በማድረግም ይታወቃሉ። ምንጭ ዘሚረር፣ ቢንስፖርት እና ስካይ ስፖርትን ተጠቅመናል።
በምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
