
ባሕር ዳር: ጥቅምት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነትን እና የፍትሕ ዘርፉን ለማዘመን በጀመራቸው የለውጥ ሥራዎች ዙሪያ ከጠበቆች ጋር ምክክር አድርጓል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያከናወናቸውን የሪፎርም እና የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል
የዳኝነት እና የፍትሕ አገልግሎትን ለማዘመን በጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው ገልጸዋል።
ጠበቆች የጥብቅና አገልግሎትን በታማኝነት የመሥራት እና ለፍትሕ አጋዥ የመኾን ግዴታ አለባቸው ነው ያሉት።
የዳኝነት አገልግሎት እና የፍትሕ ዘርፉንም በመሠረታዊነት ለመለወጥ የተጀመሩ ሥራዎችን ማገዝ እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ ጠበቃ በሪሁን አዱኛ ጠበቆች የፍትሕ ሥርዓቱ ዋና አጋር አካላት መኾናቸውን ገልጸዋል።
ጠበቆች በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ሚናቸው የሚጀምረው ደንበኞቻቸው ስለሕጉ እንዲያውቁ በማድረግ ነው ብለዋል።
ለፍትሕ ሥርዓቱ አጋዥ በመኾን አቅም ለሌላቸው ወገኖችም ነጻ የሕግ ድጋፍ የማድረግ ኀላፊነት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እየተገበረው የሚገኘው የዲጂታላይዜሽን አሠራር የፍትሕ ሥርዓቱን በማዘመን ለጠበቆች ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም አብራርተዋል።
በቴክኖሎጂ በመደገፍ የችሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየተሠራ ያለው ሥራ ፍትሕን ለማረጋገጥ ሚናው ከፍተኛ ነውም ብለዋል።
ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊ ጠበቃ ጀንበሬ ወርቄ እንደተናገሩት ፍርድ ቤቶች ቴክኖሎጅን መጠቀም መጀመራቸው የዳኝነት ሥርዓቱን የሚያሳልጥ ነው።
ሥራው በመረጃ አያያዝ ጉድለቶች የሚያጋጥሙ ችግሮችን ይፈታል ነው ያሉት።
በዘርፉ ጥናት እና ምርምር ለማድረግም የመረጃ ተደራሽነትን እንደሚያሰፋ ጠቁመዋል። ብልሹ አሠራርን በማስቀረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ነው ያሉት።
ጠበቆች ማስረጃን፣ ሕግን እና ሥነ ምግባርን መሠረት ያደረገ ሥራ በመሥራት ለፍትሕ ሥርዓት ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
ጠበቃ ታደሠ መኮነንም ዜጎች በየ አካባቢያቸው ኾነው የዳኝነት አገልግሎትን እንዲያገኙ የተጀመረው ሥራ የሚያሥመሠግን ነው ብለዋል።
የተጀመረው የዲጂታላይዜሽን ሥርዓት ዜጎች ቀልጣፋ እና የተፋጠነ ፍትሕ እንዲያገኙ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
ጠበቆችም ቦታ ሳይገድባቸው ባሉበት ኾነው ለደንበኞቻቸው አገልግሎት ለመስጠት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ጠበቆች በተቀመጠው የሕግ ማዕቀፍ መሠረት ሥራቸውን ከሠሩ ፍትሕን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝ ነው የተናገሩት።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያከናወናቸውን የቢሮ እድሳት፣ የሪፎርም እና የዲጂታላይዜሽን ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
