
በኮሮናቫይረስ የተያዘ ግለሰብ በደብረታቦር እስካሁን ባይገኝም እንደሀገር የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸው እና በበሽታው እንደተያዘ በሕክምና ከተረጋገጠ ሰው ጋር ንክኪ የሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በቫይረሱ ተይዘው መገኘታቸው በሽታው ምን ያክል በኅብረተሰቡ ዘንድ እንደተሠራጨ አመላካች በመሆኑ ነው ናሙና መውሰድ የተጀመረው።
ይህን አስመልክቶም የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ለበሽታው ተጋላጭ ይሆናሉ ተብለው የተገመቱ ቦታዎች ላይ ከትናንት ጀምሮ የኮሮናቫይረስ በሽታን ለመመርመር ናሙና እየወሰደ ይገኛል።
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ማርዬ እንግዳየሁ ለአብመድ እንደተናገሩት ከዚህ በፊት የቤት ለቤት አሰሳ በማድረግ የበሽታው ምልክት የታየባቸውን ሰዎች ወደ ጤና ተቋማት በመውሰድ ምርመራ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በመናኸሪያዎች እና ወደ ዞኑ መግቢያ በሮች ላይ የሙቀት ልኬታ እየተደረገ መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ እንደ ሀገር በሽታው እየተስፋፋ በመምጣቱና የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ሰዎች በበሽታው ተይዘው በመገኘታቸው ተጋላጭ ይሆናሉ ተብለው በታሰቡ ቦታዎች ላይ ከሚሠሩ ሰዎች የኮሮናቫይረስ በሽታን ለመለየት የሚያስችል ናሙና እየተወሰደ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ናሙና የሚወስድባቸው ቦታዎችም ትላልቅ ሆቴሎች፣ መናኸሪያዎች፣ የገበያ ቦታዎች፣ ሆስፒታሎች እና የፀጥታ አካላት እና የጎዳና ተዳዳሪዎች የሚኖሩባቸው አካባቢዎች መሆናቸውንም አቶ ማርዬ ተናግረዋል። እስካሁንም ከ82 ሰዎች ናሙና እንደተወሰደ ተናግረዋል።
በቀጣይም በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች እና ሌሎችም ከተማ አስተዳደሮች ናሙና የመውሰድ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ማርዬ አስታውቀዋል።
ናሙና የተወሰደላቸው ግለሰቦችም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምልክቶች ሳይታዩ በሽታው ከሰው ወደ ሰው እየተላለፈ በመሆኑ ናሙና በፈቃደኝነት እየሰጡ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ተጋላጭ ከሆኑ ሰዎች ናሙና መውሰዱ ራስን አውቆ ወደፊት የበለጠ ጥንቃቄ ለማድረግ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ አማረ ሊቁ -ከደብረ ታቦር
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡