“የጎንደር አብያተ መንግሥታት ዳግም ተወልደው እያበሩ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

3

ባሕር ዳር: ጥቅምት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጥገና የተደረገለትን የጎንደር አብያተ መንግሥታት መርቀው መክፈታቸው እና በከተማዋ የተሠሩ የልማት ሥራዎችን መመልከታቸው ይታወሳል።

የጎንደር የልማት ሥራዎችን አስመልክተው መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ኢትዮጵያ ብዙ ታሪክ አላት፤ በተለይም የሰሜኑ ክፍል አብያተ መንግሥታት በስፋት የሚገኙበት ነው ብለዋል።

ከአሁን በፊት በቱሪዝም ፍሰት ይታወቅ የነበረው የሰሜኑ ክፍል እንደነበር ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ላይ ግን በሌሎች የሀገሪቱ አቅጣጫዎች ለቱሪዝም መስህብ የሚኾኑ በርካታ ሃብቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሁሉንም አካባቢዎች በማየት እና በመጎብኘት ከዚህ በፊት የነበሩ ቅርሶች፣ የኢትዮጵያ ታሪኮች ለትውልድ እንዲቀጥሉ እና ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር እንደኾነች ማረጋገጫ የሚኾኑ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።

ከአሁን ቀደም የነበሩ መሪዎች ይህ ቅርስ አለን፣ አባቶቻችን የሠሩት ነው ብለው አያውቁም ነበር ነው ያሉት። የጎንደር አብያተ መንግሥታት የዓለም ቅርስ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ፈረሰ ማለት የዓለም ቅርስ እንዳጣን የሚወሰድ ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ወደ ጎንደር ሲሄዱ መጀመሪያ ያዩት የጎንደር አብያተ መንግሥታትን ነው፣ ቅርሱን ለመጠገን የወሰኑትም ወዲያው እንዳዩት ነው ብለዋል።

ቅርሱን ለመጠገን በነበረው ሂደት የውጭ እና የውስጥ ፈተናዎች እንደነበሩም አስታውሰዋል። ይህን ቅርስ አትንኩት፤ ከነካችሁት ይፈርሳል፤ ዝም ብሎ ይቀመጥ የሚል ተጽዕኖ ነበር፤ በሀገር ውስጥ አቅም አይቻልም የሚል አስተሳሰብም ነበር፤ ይህ ሁሉ ታልፎ ቅርሱ ተጠግኗል ብለዋል።

ቅርሱ ተጠገነ ብቻ ሳይኾን እንደገና ተወለደ ማለት ይቻላል ነው ያሉት። የጎንደር አብያተ መንግሥታት በአጭር ጊዜ የተጠገነ መኾኑንም ገልጸዋል። ይህ ጥገና ሀገራችን መሥራት እንደምትችል ያሳየችበት ነው ብለዋል። ጥገናው በራስ አቅም የተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

የጎንደር አብያተ መንግሥታት ጥገና ታሪክን የማስቀጠል እና የነበረውን ለልጆቻችን የማስተላለፍ ነው ብለዋል። እንደዚህ አሳምረን ታሪካችንን ማስቀጠላችን ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር እንደነበረች፤ አሁንም እንደኾነች እና ወደፊትም እንደምትኾን የሚያሳይ ምልክታችን ነው ብለዋል።

የፋሲል አብያተ መንግሥታት ጥገና የመቻል ልክ ማሳያ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የቀደምቶቻችን ገናናነታቸው የታተመባቸው የዚህ ትውልድ የታሪክ ኀላፊነትን የመወጣት ከፍታ የታየባቸው አብያተ መንግሥታቱ እንደ አዲስ የንጋት ጮራ ዳግም ተወልደው እያበሩ ነው” ብለዋል።

የለውጡ መንግሥት የኢትዮጵያን ሃብቶች አቧራቸውን እያራገፈ አሻራ እያተመ መኾኑንም ገልጸዋል።

የመገጭ ግድብም ረዘም ያለ ጊዜ እንደወሰደ አስታውሰዋል። የመገጭ ግድብ በታችኛው ያለውን አካባቢ ማልማት ብቻ ሳይኾን የጎንደር ከተማ ውኃን ይፈታል ተብሎ የሚታሰብ ትልቅ ግድብ ነው ብለዋል።

በመዘግየቱ ምክንያት በመፍረስ ላይ የነበረ ሥራ ነው፤ እንደገና እንደ አዲስ እየተሠራም ነው፤ በጥሩ ሁኔታ ላይም ይገኛል፤ በዚህ ዓመትም ይጠናቀቃል ብለን እናስባለን ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጥገናው የጎንደርን ትንሳዔ ከ400 ዓመታት በኋላ የሚያሳይ ነው” አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
Next articleጠበቆች የጥብቅና አገልግሎትን በታማኝነት የመሥራት እና ለፍትሕ አጋዥ የመኾን ግዴታ አለባቸው።