
ባሕር ዳር: ጥቅምት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጥገና የተደረገለትን የጎንደር አብያተ መንግሥታት መርቀው መክፈታቸው እና በከተማዋ የተሠሩ የልማት ሥራዎችን መመልከታቸው ይታወሳል።
የጎንደር ከተማ ቆይታቸውን አስመልክተው መልዕክት ያስተላለፉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ስለ ጎንደር ብዙ ነገር ማለት እችላለሁ፤ ብዙ ሃብት እያለው ነገር ግን ሁሉን ነገር አጥቶ የቆየ ነው ብለዋል።
ያለፉት መሪዎች እኔን ጨምሮ ማድረግ የሚገባንን እያደረግን አልነበረም፤ ያለፉት መንግሥታት ለጎንደር የሚገባትን ትኩረት አልሰጡም ነበር ነው ያሉት።
ጎንደር ጥንታዊት ከተማ ናት፤ በሀገራችን የሀገረ መንግሥት ግንባታ የጎንደር ዘመን የራሱን አስተዋጽኦ አድርጎ አልፏል ብለዋል። ከለውጡ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሀገራችንን የተፈጥሮ ሃብት፣ ሊጎበኙ የሚገባቸውን ቀርሶችን ገልጦ የማሳየት ሃሳብ የጎንደር ከተማን ገልጦ ማሳየት ችሏል ነው ያሉት።
የጎንደር አብያተ መንግሥታት ዐይናችን እያየ ሊፈርስ ነበር ያሉት አፈ ጉባኤው ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ውርደት ነበር የሚኾነው፤ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ቅርስ በፍጥነት ካልደረስንለት አደጋ ላይ ነው ብለው በተሠራው ሥራ በሚገባ ተጠግኗል ነው ያሉት።
ከቤተ መንግሥቱ ሥር ያደግን ሰዎች ስለኾንን እና የምናውቀው ስለኾነ ቅርሱ በመፍረስ አደጋ ላይ ነበር ብለዋል። አሁን ግን ዳግም ተወልዷል ነው ያሉት።
የጎንደር አብያተ መንግሥታት በዚያ ልክ በመጠገናቸው ደስተኛ መኾናቸውንም ተናግረዋል። የጎንደር ሕዝብም ደስተኛ መኾኑን ገልጸዋል። ቅርስነቱ ተጠብቆ ለጎብኝዎች በሚመች ሁኔታ ጥገናው ተጠናቅቆ ደረጃውን የጠበቀ የቱሪዝም መዳረሻ መኾኑንም ተናግረዋል።
ይህ ጥገና የጎንደርን ትንሳዔ ከ400 ዓመታት በኋላ የሚያሳይ ነው ብለዋል። በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ተስፋ ሰጭ መኾናቸውንም አንስተዋል። የጎንደር ከተማን ጥንታዊነት በጠበቀ መልኩ ለተሠራው ሥራ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር መሪዎችን አመሠግናቸዋለሁ ነው ያሉት።
የመገጭ ግድብ ለረጅም ጊዜ የመዘግየት ችግር ስለነበረበት በወቅቱ አለመጠናቀቁን አስታውሰዋል። ከባለፈው አንድ ዓመት በኋላ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት የመገጭ ግድብ የተሻለ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል። የመገጭ ግድብ ለጎንደር ከተማ እና አካባቢው ትልቅ ተስፋ እንዳለውም ገልጸዋል። ትልቅ ልማት ይዞ የሚመጣ እና የጎንደርን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግር የሚፈታ እንደኾነም ተናግረዋል።
የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትም ሌላው የሚያስደንቅ ሥራ መኾኑን ገልጸዋል። አካባቢው ትልቅ የኾነ የቱሪዝም መዳረሻ መኾኑንም ተናግረዋል። ጎርጎራ እና ባሕር ዳርን የሚያገናኝ ዘመናዊ የባሕር ላይ ትራንስፖርት መዘጋጀቱንም ገልጸዋል። ይህ ደግሞ የጎብኝዎችን ፍሰት ይጨምራል ነው ያሉት።
የቱሪዝም እንቅስቃሴው ከአዲስ አበባ ዓባይ፣ ከዓባይ ባሕር ዳር፣ ከባሕር ዳር ጎርጎራ፣ ከጎርጎራ ጎንደር ስሜን ተራራዎች የሚያስሄድ ነው ብለዋል። የሀገርን ገጽታ የሚቀይር መኾኑንም ተናግረዋል። በጎንደር ከተማ እና አካባቢው በተሠሩ ሥራዎች በጣም ተደስቻለሁ ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
