“የጎንደር አብያተ መንግሥታት የማንነታችን መገለጫ ናቸው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

4

ባሕር ዳር: ጥቅምት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጥገና የተደረገለትን የጎንደር አብያተ መንግሥታት መርቀው መክፈታቸው እና በከተማዋ የተሠሩ የልማት ሥራዎችን መመልከታቸው ይታወሳል።

በጎንደር ከተማ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የጎንደር አብያተ መንግሥታት ላለፉት 400 ዓመታት የቆዩ መኾናቸውን ገልጸዋል።

አብያተ መንግሥታቱ የሥልጣኔያችን መገለጫ ናቸው ብለዋል። በዚያ ዘመን የኪነ ሕንጻ ብቻ ሳይኾን የድልድይ እና የመንገድ ድልድይ ግንባታ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው መኾኑን ተናግረዋል።

የጎንደር አብያተ መንግሥታት የማንነታችን መገለጫ የቱሪስት መስህብ ናቸው ብለዋል። የጎንደር አብያተ መንግሥታት መጠገን ለጎንደር፣ ለአማራ ክልል እና ለመላው ኢትዮጵያ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ ከኾኑ አካባቢዎች መካከል የጎንደር አብያተ መንግሥታት ቀዳሚዎች ናቸው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ጥገና መደረጉ የጎንደር አብያተ መንግሥታት ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ እንደሚያሳድግም ገልጸዋል።

የመገጭ ግድብ ተጓትቶ መቆየቱን ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት ጀምሮ በመንግሥት ቁርጠኛ ውሳኔ ግንባታው እየተፋጠነ መኾኑን ገልጸዋል። አሁን ላይ በጥሩ ሂደት ላይ ነው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ነው፤ መገጭ በሚጠናቀቅበት ጊዜ ለአካባቢው አርሶ አደሮች በመስኖ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል፤ ለጎንደር ከተማ ሕዝብም የመጠጥ ውኃ አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።

የመገጭ ግድብ በጎንደር ከተማ ያለውን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግር በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሻሽለውም ገልጸዋል። የመገጭ ግድብ ከመስኖ ልማት እና ከንጹሕ መጠጥ ውኃ ባሻገር ጥቅም እንዳለውም ተናግረዋል።

ሲጓተት የነበረው የአዘዞ ጎንደር የመንገድ ፕሮጀክት በከፍተኛ ጥራት እና ፍጥነት እየተጠናቀቀ መኾኑንም አመላክተዋል። የመንገድ ፕሮጄክቱ መጠናቀቅ የትራንስፖርት አገልግሎቱን በማሳለጥ የከተማዋን ነዋሪዎች የሥራ ቅልጥፍና የሚያሻሽል ነው ብለዋል። የከተማዋን ውበት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሻሽልም አንስተዋል።

የኮሪደር ልማት የከተሞች ትንሳኤ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የከተሞችን እንቅስቃሴ የሚያቀላጥፍ፣ ውበትን የሚጨምር፣ የከተሞችን የቱሪዝም ፍሰት እና የንግድ እንቅስቃሴ የሚጨምር መኾኑንም ተናግረዋል። አብያተ መንግሥታቱ፣ የኮሪደር ልማቱ፣ የመገጭ ግድብ እና ሌሎች የልማት ሥራዎች ጎንደር ከተማን የቱሪዝም መዳረሻ እና የንግድ ማዕከል የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ጎንደር ተሞሽራለች ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ይህ ሥራ የመጀመሪያው እንጂ የመጨረሻው አይደለም፤ ለሌሎች ሥራዎች መትጋት እንደሚያስፈልግ መልዕክት የተላለፈበት መኾኑንም ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ከጎንደር ከተማ ባሻገር በሌሎች ከተሞችም የኮሪደር ልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። በየከተሞች እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች የአማራ ክልልን የልማት ሥራ ከፍ የሚያደርጉ እና ተጨማሪ ሃብት የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል። በተሠሩ ሥራዎች ደስተኛ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአዲስ የቱሪዝም ገጽታን የፈጠረው የጎንደር አብያተ መንግሥታት ቅርስ
Next articleየኮሪደር ልማት ሥራዎች ተጨባጭ ልማትን እንዳመጡ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።