አዲስ የቱሪዝም ገጽታን የፈጠረው የጎንደር አብያተ መንግሥታት ቅርስ

12

ባሕር ዳር: ጥቅምት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በታሪካዊነቱ እና በኪነ ሕንጻ ጥበቡ ብዙዎች ተደምመውበታል። ነገሥታት ዙፋናቸው አድርገው ታሪክ ሠርተውበታል፣ አሻራቸውን አስቀምጠው ለትውልድ አሥተላልፈውበታል። ነገሥታት ከነሙሉ ክብራቸው ተሰይመው ሀገር አስተዳድረውበታል።

የኢትዮጵያን ጽኑ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ በተግባር አሳይተውበታል፣ የወርቃማው የጎንደር ዘመን መገለጫ ህያው መስክር ኾኖ ትውልዶችን ተሻግሯል። የሥልጣን፣ የኪነ-ጥበብ እና የሃይማኖት ማዕከል ኾኖም ለዘመናት አገልግሏል የጎንደር አብያተ መንግሥታት ሕንጻ።

ኢትዮጵያውያን በዘመኑ የነበራቸውን የሀገር በቀል ዕውቀት፣ የኪነ ሕንጻ ጥበብ፣ የቀደምት ሥልጣኔ እና የአዕምሮ ልዕልና ከፍ አድርጎ የሚያሳይ ህያው አስረጅ ስለመኾኑም ያዩት ሁሉ ይመሠክራሉ። በቀደሙት ትውልዶች ተገንብቶ ለተተኪው ትውልድ ቅርስ ኾኗል። በአስደናቂነቱም ከኢትዮጵያ አልፎ በዩኔስኮ የዓለም አቀፍ ቅርስነት ተመዝግቧል።

ለጎንደር ከተማ ምልክት፣ የነዋሪዎቿ መታወቂያ እና የኩራት ምንጭ የኾነው ይህ አብያተ መንግሥታት ባሳለፈው ረጅም ዕድሜ ምክንያት የመፍረስ አደጋ ተደቅኖበት ቆይቷል። እንደ አይናቸው ብሌን በስስት የሚመለከቱተ ነዋሪዎችም ቅርሱን ከጉዳት ለማዳን ጥሪ ሲያቀርቡ ኖረዋል።

ይህንን ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አነሳሽነት የጥገና ሥራ ሲሠራ ቆይቶ ከሰሞኑ ለምረቃ በቅቷል፣ ለሕዝብ ዕይታም ክፍት ኾኗል።

የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር) የጎንደር አብያተ መንግሥታት ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት በቀዳሚነት ካስመዘገበቻቸው ቅርሶች መካከል አንዱ መኾኑን ይናገራሉ። መልከ ብዙ ባሕላዊ እና ታሪካዊ ጸጋዎችን የያዘ ቅርስ ስለመኾኑም ያስረዳሉ።

ቅርሱ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ በመኾኑ የመፍረስ አደጋ ተደቅኖበት መቆየቱን አንስተዋል። አሁን ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) አነሳሽነት እና የቅርብ ክትትል ጥገና ተደርጎለት መጠናቀቁ በሕዝቡ ሲነሳ የነበረውን ቅርሱን የማጣት ስጋት የቀረፈ መኾኑን ገልጸዋል። ለዘመናት ሲነሳ የነበረውን ጥያቄ የመለሰ ነውም ብለዋል።

የቅርስ ጥገናው ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ የተከናወነ ስለመኾኑም አብራርተዋል። ተቆርቋሪ በኾነ የሀገር በቀል ሥራ ተቋራጭ ተይዞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅርብ ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገለት የተከናወነ ነው ብለዋል። በቅርስ ጥገና የሚታወቁ፣ የረጅም ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች በቅርበት እየተከታተሉ፣ እያማከሩ እና አብረው እየሠሩ ጥገናው በጥንቃቄ የተከናወነ ስለመኾኑም አስረድተዋል።

የቅርስ ጥገናው ለትውልድ ማነጽ እና ለማኀበረሰብ ግንባታ ተምሳሌት የሚኾን ነው ብለዋል። የዛሬ ሥራ የነገ ቅርስ ነው ያሉት ዶክተር አየለ ቀጣዩ ትውልድ ከቀደምት አባቶቹ በመማር ዘመን ተሻጋሪ የኾነ የራሱን ታሪክ እንዲሠራ የሚያነሳሳ ስለመኾኑም ነው ያስረዱት።

ቅርሱን ከመጠገን ባለፈ ተጨማሪ የቱሪዝም እሴቶችን ይዞ የመጣ ስለመኾኑም አንስተዋል። አጠቃላይ ግቢውን በማስዋብ ለቱሪስት በሚመች መልኩ አዲስ ገጽታን የፈጠረ ነው ብለዋል።

ቅርሱ ከመጠገኑ በፊት በቀን ብቻ የሚጎበኝ እንደነበር አስታውሰው አኹን ላይ ግን 24 ሰዓት የሚጎበኝ ኾኗል ነው ያሉት። ለዚህም ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ መብራቶች የተገጠሙለት ስለመኾኑም አብራርተዋል።

በሌሎች ዓለማት የተለመደውን የምሽት የጉብኝት እንቅስቃሴ በሀገር ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ ዕድል የሚፈጥር መኾኑንም ነው የጠቆሙት። ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ ማሟላት የሚገባቸውን ሁሉን አቀፍ መሠረተ ልማቶች የተሟሉለት ስለመኾኑም ነው የገለጹት።

የቅርሱ ጥገና ተጠናቅቆ ለቱሪስት ክፍት መደረጉ በክልሉ ካሉት ዋና ዋና የቱሪስት መዳረሻዎች ጋር በማስተሳሰር ክልሉን የጎብኝዎች ማዕከል እንዲኾን ያስችለዋል ነው ያሉት። የቱሪስቶችን ቆይታ በማራዘምም ለክልሉ የቱሪዝም ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫዎት አመላክተዋል።

ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የጎንደር አብያተ መንግሥታት የማንነታችን መገለጫ ናቸው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next article“የጎንደር አብያተ መንግሥታት የማንነታችን መገለጫ ናቸው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ