ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የጎንደር አብያተ መንግሥታት ጥገናን መርቀው ከፈቱ።

1

ባሕር ዳር: ጥቅምት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች የተጠገነውን የጎንደር አብያተ መንግሥታት መርቀዋል።

የተከናወነው ሰፊ የእድሳት ሥራ በቅርስ ስፍራው ነባሩን ታሪክ በመጠበቅ ውበቱን እና ተደራሽነቱን በማሻሻል አዲስ እስትንፋስ የሰጠ ኾኗል።

የጥገና ሥራው የቤተ መንግሥቱን የግንባታ መዋቅር መጠገን፣ የእግረኛ መንገዶችን ማሻሻል፣ ቁልፍ የሆኑ ሕንፃዎችን ከዝግባ እና ዋንዛ በባሕላዊ ቁሳቁሶችን ተጠቅሞ በማደስ የስፍራውን ግለ ወጥ መልክ እና ባሕርይ ለመጠበቅ ተሰርቷል።

ለጎብኝዎች ምቾት የተሰናዱ አገልግሎት መስጫዎችም ትርጉም ባለው ደረጃ ተሻሽለዋል። አዲስ የቱሪስት ማዕከልም ተከፍቷል። ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶች፣ የተሻሻሉ የመብራት እና የደኅንነት ሥርዓቶችም ተሰናድተዋል።

እንደ አጼ ፋሲል፣ አጼ ቀዳማዊ ዮሃንስ እና አጼ ቀዳማዊ ኢያሱ አቢያተ መንግሥት ብሎም ድልድዮች፣ መታጠቢያ ሥፍራዎች፣ ታሪካዊ በሮች ወዘተ በጥንቃቄ ታድሰዋል።

በተጨማሪም ከ40 ሺህ ስኩየር ሜትር በላይ የአካባቢው ምድር የማስዋብ ሥራ ተሰርቷል። ይኸም ለጎብኝዎች ይበልጥ ሳቢ የሆነ ከባቢ ፈጥሯል። አጠቃላይ የእድሳት ሥራው ከአንድ ዓመት በታች የፈጀ ሲሆን የዚህን አስደናቂ የታሪክ እና የባሕል ሥፍራ ለረዥም ጊዜ ጠብቆ በሚያቆይ አኳኋን ተከናውኗል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ትናንትናችን ማስታወሻችን እና መታወሻችን ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleየፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች የልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው።