
ባሕር ዳር: ጥቅምት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የታደሰውን የጎንደር አብያተ መንግሥታት መርቀው ከፍተዋል።
በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክትም “የዚህ ታላቅ ታሪክ አካል ለመኾን ዕድል ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ” ብለዋል። ፋሲል በእጃችን ስለኾነ የረከሰ ወርቅ ነው፤ ብንዞር ብንዞር በቀላሉ የማናገኘው፣ በእጃችን ያለን የማርከስ ክፉ አባዜ ስላለብን የረከሰ ትልቅ ወርቅ እንደኾነ ነው የገለጹት።
ይሄን የመሰለ ስጦታ የሰጡን አባቶቻችን ፈለግ ተከትለን ሀገር ብናለማ፣ ሀገር ብንሠራ ዛሬ ኢትዮጵያ ተረጅ እና ለማኝ አትኾንም ነበር ነው ያሉት። ትልቁ ችግራችን እናንስና ትልቁን ጎትተን በማሳነስ፣ መተካከል እንፈልጋለን ብለዋል።
ከእነዚህ ታላላቅ መሪዎች በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ያጋጠመው ችግር ያነሱ፣ ትላልቁን ደግሞ ጎትተው የሚያሳንሱ ተበራክተው እንደኾነ ነው የገለጹት።
ታላቆችን ማክበር፣ የታላቆችን ሥራ ማድነቅ፣ የታላቆችን ሥራ መመርመር ሲጀመር በዚያ ሥራ ላይ አንድ ጡብ ባስቀምጥ መባሉ አይቀርም፤ ታላላቆችን ማሳነስ ስንጀምር ግን የማናድግ፣ ያደገውን የምናሳንስ፣ ተያይዘን የምናጥር ነው የሚያደርገን ብለዋል።
“ትናንትናችን ማስታወሻችን እና መታወሻችን ነው፤ ሰው ማስታወሻውን፣ መታወሻውን አይዘነጋም፣ አያጠፋም፣ ሁላችን ዕድሜያችን ከፍ እያለ በሄደ ቁጥር መለስ ብለን እድገታችንን፣ አስተዳደጋችንን እና ጎረቤቶቻንን እናስታውሳለን” ብለዋል።
ኋላውን ማስታወስ የሁሉም ሰው ተፈጥሯዊ ልማድ ነው፤ ኋላውን ማስታወስ የቻለ ማኅበረሰብ ዛሬን ለመነሻነት፣ ለመሥሪያነት ይገለገላል፤ ዛሬን መነሻ ያላደረገ ነገን ማየት አይችልም ነው ያሉት።
በጎንደር ከተማ እና በፋሲል ግቢ ውስጥ ያየሁት ለውጥ ልጆቻችን ከእኛ የተሻለ ተስፋ እንዳላቸው የሚያሳይ ነው ብለዋል። የጎንደር ልጆች ከፊታችሁ ያለው ዘመን ብሩህ ዘመን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አባቶቻችሁ ገንብተውታል፤ እኛ ለማቆየት ሞክረናል፤ አስበልጣችሁ ጎንደርን ብትሠሩ የበለጠ የለማ ሀገር ለመፍጠር ያስችላል ነው ያሉት።
የጎንደር ልጆች ልቦናቸውን ሰብሰብ አድርገው ጎንደርን በድጋሜ ለመውለድ እንዲሠሩም አሳስበዋል። ፋሲል አልታደሰም፤ ፋሲል አልተጠገነም፤ ፋሲል ዳግም ነው የተወለደው ብለዋል። በአብያተ መንግሥታቱ አካባቢ ያሉ አካባቢዎች ዳግም መወለድ እንዳለባቸውም ተናግረዋል። ጎንደር ዳግም ተወልዳ ማየት የሁላችን መሻት መኾን አለበት ነው ያሉት።
ከአዘዞ እስከ ፒያሳ ድረስ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ጎንደር ዳግም ለመወለድ እያማጠች እንደኮነ ያሳያል ብለዋል። ምጡ ሐኪም እና ሙያተኛ ይጠይቃል፤ አሁን ባለበት ከቀረ ግን ይጨነግፋል አይወለድም ብለዋል። ደግፈን፣ አግዘን እንዲወለድ ካደረግነው ግን በቤተ መንግሥቱ እንደታየው ውበት ሁሉ በመላ ጎንደር ይታያል ነው ያሉት።
ለጎንደር የመጣውን ዕድል መጠቀም እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ዕድል መጠቀም የብልሆች፣ የአዋቂዎች፣ የአስተዋዮች፣ የጥበበኞች ልምምድ ነው፤ ጎንደርን በመሥራት ጉዳይ ሁላችን የጋራ አቋም ይዘን መሥራት አለብን ብለዋል።
ከጎንደር ጎርጎራ ለመሄድ ጎንደሬዎች በወታደር ተጠብቀው እየሄዱ እንዴት ልማት ሊሠራ ይችላል፣ ባዕድ ሳይኾን ባለ ሀገሮች፣ ባለቤቶች ከአንድ አካበቢ ወደ ሌላው አካባቢ የሀገራቸውን ልማት ማየት ማገዝ እንዲችሉ ሰላም ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በአካባቢው ወደ ጫካ የወጡ ወንድሞች ጊዜ ማባከን እንደማይገባቸው እና በትብብር መሥራት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
በጋራ መሥራት እና ሰላምን ማምጣት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ጎንደሬዎች ጎንደርን ዳግም እንዲወልዱም አሳስበዋል። ተባብረው እንዲሠሩም አስገንዝበዋል። ጎንደር ታሪካዊነቷን እና ጥንታዊነቷን ሳትለቅ ለዓለም አሸብራቂ ከተማ እስክትኾን ድረስ በትጋት እንዲሠሩ አሳስበዋል።
ጉልበት ይሸሻል፤ ጊዜ ይሸሻል፤ ሥልጣን ይሸሻል፤ ሁሉም አላፊ ነው፤ የማያልፈው እንዲህ አይነቱ ታላቅ ሥራ ነው እና ታላቅ ሥራ በጋራ እንድንሠራ አደራ ልላችሁ እወዳለሁ ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
