ለተማሪዎች ምገባ ሥርዓት በትኩረት እየሠራ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

5
ደብረ ማርቆስ: ጥቅምት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በትምህርት ቤቶች የተማሪ ምገባ ሥርዓት በመዘርጋት የትምህርት ተሳትፎ እና የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ አስታውቋል።
የዞኑ ትምህርት መምሪያ በ2018 የትምህርት ዘመን ለተማሪዎች ምቹ የትምህርት ቤት አካባቢ ለመፍጠር ትኩረት ከሰጣቸው ተግባራት መካከል የተማሪዎች ምገባ ሥርዓትን መዘርጋት አንዱ እና ዋናው ነው።
ትምህርት በተጀመረባቸው ትምህርት ቤቶች ምገባ በማካሄድ እና ለተማሪዎች ምቹ ኹኔታ ለመፍጠር እየተሠራ መኾኑን የተናገሩት የመምሪያው ኀላፊ ጌታሁን ፈንቴ ናቸው።
ለተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ከመንግሥት እና ከማኅበረሰቡ ተሳትፎ ከ58 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦ ወደ ሥራ መገባቱንም መምሪያ ኀላፊው ተናግረዋል።
የምገባ ሥርዓቱ የትምህርት ተሳትፎን እና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ትልቅ ፋይዳ አለው ያሉት መምሪያ ኀላፊው ተግባሩን ከትምህርት ቤት እስከ ዞን በተደራጀ መልኩ በመምራት ተጠቃሚ የሚኾኑ ተማሪዎች ተለይተው አስፈላጊ ግብዓቶችን ለማሟላት እየተሠራም እንደኾነ ነው የገለጹት።
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያነጋገራቸው የጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በድሉ አንማው በወረዳው ባሉ 14 ትምህርት ቤቶች ከ2 ሺህ 600 በላይ ተማሪዎች ተለይተው የምገባ ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።
በትምህርት ዘመኑ ለተግባሩ ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቧል ነው ያሉት። የትምህርት ቤት ምገባ ሥርዓት ተማሪዎች በትምህርታቸው ንቁ ተሳታፊ ኾነው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል።
ሌላው አሚኮ ያነጋገራቸው የአዋበል ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አበባው ጫኔ የወረዳው አሥተዳደር ምክር ቤት የመማር ማስተማሩ ሥራ ውጤታማ እንዲኾን ከፍተኛ የበጀት ድጋፍ እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
የትምህርት ቤት ምገባ አሠራር የበለጠ ውጤታማ እንዲኾን የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየተሳሳቱ መረጃዎችን መከላከል እና እውነተኛ መረጃን ማጣራት ይገባል።
Next article“ትናንትናችን ማስታወሻችን እና መታወሻችን ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)