የተሳሳቱ መረጃዎችን መከላከል እና እውነተኛ መረጃን ማጣራት ይገባል።

8
ባሕር ዳር: ጥቅምት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ከዩኤን ዲፒ ፒስ ሳፖርት ፋሲሊቲ ጋር በመተባበር ለሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን አመራሮች እና ባለሙያዎች የተሳሳቱ መረጃዎችን በመከላከል እና እውነተኛ መረጃን በማጣራት ዙሪያ ያተኮረ የሥልጠና መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ የተገኙት የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ደጀኔ ልመንህ ቢሮው የተሳሳቱ መረጃዎችን በመከላከል እና እውነተኛ መረጃን በማጣራት በኩል እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከሚዲያ አካላት ጋር እየተወያየ ነው ብለዋል። የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ምክክር እና ሥልጠናው አስፈላጊ መኾኑንም ተናግረዋል።
መገናኛ ብዙኅንን በዓለም አቀፍ ደረጃም ኾነ በሀገር አቀፍ ደረጃ በትክክለኛው መንገድ ስንጠቀምበት ግለሰብን፣ ቡድኖችን፣ ሕዝብን እና ሀገርን ወደ ትክክለኛ መንገድ ይመራል ብለዋል። በተሳሳተ መንገድ ስንጠቀም ደግሞ አደጋ ላይ ይጥላል ብለዋል።
ሚዲያን በተሳሳተ መንገድ የተጠቀሙ ሀገራት ወደ እርስ በእርስ ግጭት በመግባት ሰፊ የደም መፋሰስ እና የኢኮኖሚ ውድመት ገጥሟቸዋል።
ዛሬ ላይ በሀገራችን ብሎም በክልላችን የምናየው የተሳሳተ መረጃ ያልኾነውን እንደኾነ፣ የኾነውን ደግሞ እንዳልኾነ በማናፈስ ሕዝብን ለማደናገር ሲሞክሩ ይታያል ነው ያሉት።
በቀጣይ ከዚህ የሥልጠና መድረክ ከፍ ያለ ግንዛቤ በመውሰድ የሀሰተኛ መረጃዎችን በማጣራት ትክክለኛ መረጃዎችን ለማኅበረሰቡ የማዳረስ ሥራ መሥራት ይገባናል ብለዋል።
በመድረኩ የተለያዩ የቢሮ ኀላፊዎች፣ አመራሮች እና የሚዲያ አካላት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous article“የአፍሪካ ምልክት፤ የጥቁሮች አብነት”
Next articleለተማሪዎች ምገባ ሥርዓት በትኩረት እየሠራ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።