
ባሕር ዳር: ጥቅምት 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አፍሪካውያን የነጻነታቸው አብነት፣ የሉዓላዊነታቸው ምልክት አድርገዋት ኖረዋል፤ ጥቁሮች ኮርተውባታል፤ መመኪያችን፣ አለኝታችን ብለዋታል።
በጠነከረ መሠረት ላይ የታነጸ ቤት ዝናብ ቢዘንብ፣ ጎርፍም ቢጎርፍ፣ ነፋስም ቢነፍስ፣ ገፍተው ሊጥሉት አይችሉም እንደተባለ እርሷ መሠረቷን ያጸናች፤ ነጻነቷን ያስጠበቀች፤ ሉዓላዊነቷን ያስከበረች፤ ማንነቷን ያልለቀቀች፤ ባሕል እና ሃይማኖቷን፣ ታሪክ እና እሴቷን ይዛ የኖረች ናት ኢትዮጵያ።
ኢትዮጵያ ከትናንት እስከ ዛሬ ያለ ፈተና የኖረችበት፣ ያለ ጠላት ያደረችበት ጊዜ የለም። በፈተና እያለፈች፣ በመከራ እየጸናች ነው። ለአፍሪካውያን “ምልክት፣ ለጥቁሮች አብነት” ኾና የኖረችው።
ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን ፊታውራሪ ናት። የዓለም የታሪክ፣ የፖለቲካ፣ የሥልጣኔ፣ የባሕል እና የእሴት የስበት ማዕከል ናትና በብዙዎች ዘንድ በስጋት ትታያለች።
ቀይ ባሕርን እና ዓባይን በመሰሉ ውድ ሀብቶች መካከል ላይ የጸናችው ኢትዮጵያ በእነዚህ ሀብቶች ላይ እንዳትጠቀም የሚጥሩት እና በጠላትነት የሚነሱት ብዙዎች ናቸው። ይህ ጠላትነት ደግሞ አሁን የጀመረ ሳይኾን ከጥንት እስከ ዛሬ ድረስ የቆየ ነው።
ጳውሎስ ኞኞ የኢትዮጵያ እና የኢጣሊያ ጦርነት በተሰኘው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ለሺህ ዓመታት ያህል የተደጋገመ ሙከራ ተደርጓል። ኢትዮጵያውያን ግን ሀገራቸውን በሌላ ባዕድ ሳያስይዙ ባላቸው ኃይል ሲከላከሉ ቆይተዋል።
በአውሮፓም ኾነ በእስያ፣ በአፍሪካ የሚነሱ ታላላቅ መንግሥታት ጉልበት እያገኙ ግዛታቸውን በሚያሰፉበት ጊዜ ኢትዮጵያንም ለመደረብ ብዙ ጊዜ ሞክረዋል። ኢትዮጵያውያን ግን ለማንም ላይበገሩ እና ሳይገብሩ እስካሁን ሀገራችንን አስከብረው ቆይተዋል። መለስ ብለን ከታሪካችን ውስጥ በመጠኑ ብንመለከት የሚያኮራን እና የሚያስመካን ታሪክ አለን ይላሉ።
ኢትዮጵያ ከሩቅም ከቅርብም የመጣውን ጠላት እየመከተች፤ ጠላቶቿን እያስገበረች፣ ክብሯን እያስጠበቀች የኖረች የገናና ታሪክ ባለቤት ናት።
ታሪክ ስለኢትዮጵያውያን ጀግንነት ሲመሰክር ኖሯል። ስለ ኢትዮጵያውያን አንድነት፣ ነጻነት እና አትንኩኝ ባይነት በደማቁ ከትቧል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በጦር የማይፈታ፣ በዘመቻ ጋጋታ የማይረታ፤ የሰው የማይነካ የራሱንም አሳልፎ የማይሰጥ ነው። የአፍሪካን፣ የእስያን እና የሌሎች ዓለማት ሀገራትን ያስገበሩ ኃያላን በኢትዮጵያ ላይ አቅም አልነበራቸውም፤ አልቻሉም፤ አይችሉምም። ስለ ምን ካሉ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ለጠላት አይበገሩም። ለበዓድ አይገብሩምና።
ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የሚጠብቋት ፈረሰኞች፣ የባሕር ኃይል ጀግኖች እና ሌሎች ከአንበሳ የጀገኑ ልጆች ነበሯት። ዛሬም ዘመኑን የዋጁ አናብስት አሏት።
ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን የማያስነኩ እና በጦርነትም የማይሸነፉ ሕዝቦች መኾናቸውን ወዳጅ አይደለም ጠላት ሲመሰክር ኖሯል።
ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን የማይለቁ እና የሌላ ሀገር የማይፈልጉ በመኾናቸው እንጂ እንደ ታሪክ ጸሐፊዎች መስካሪነት ከኾነ ድንበር እያለፉ የሚይዙበት ብዙ አቅም ነበራቸው ይላሉ ጳውሎስ።
ሐሪ አትክንስ የኢትዮጵያ ታሪክን በመዘገቡበት መጽሐፋቸው ኢትዮጵያ በዓለም የታወቀች እና የተፈራች ሀገር ናት። በአፍሪካ ጉዳይም ቀንደኛ መሪ ናት። ኢትዮጵያ በአፍሪካ አሕጉር የረጅም ጊዜ ነጻነቷን ጠብቃ በመኖር በታሪክ ውስጥ ዋናውን ደረጃ ይዛለች። ኢትዮጵያ አፍሪካውያን ከቅኝ ገዢዎች እንዲላቀቁ ባደረገችው ተጋድሎ የአፍሪካ ሀገራትን አሻሽላለች ብለዋል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትግላችን በተሰኘው መጽሐፋቸው የቅኝ ገዢ ኃይሎች የጥቁር ሕዝብ ነጻነት አርዓያ እና ምልክት የኾነችውን ኢትዮጵያን በማዳከም አፍሪካን ለመበጥበጥ ያላደረጉት ጥረት የለም ብለው ጽፈዋል።
ኢትዮጵያ ይህ ሁሉ ጫና እና የጦርነት ጋጋታ የሚደርስባት በቀይ ባሕር እና በዓባይ ሸለቆ እንዳትጠቀም፣ ተጠቅማም በዓለም ላይ ገናና እንዳትኾን፤ ከእነርሱ በላይም እንዳትታይ ስለሚፈልጉ እንጂ በጠላትነት ተነስታባቸው አልነበረም። አይደለምም፤ አይኾንምም።
ፕሮፌሰር ላጵሶ ጌ. ድሌቦ የኢትዮጵያ ረጅም የሕዝብ እና የመንግሥት ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ከጥንት እስከ ዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ጥያቄ ከአካባቢው ጂኦፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ።
የኢትዮጵያ የውጭ እና የጂኦፖለቲካ ግንኙነት
ከአፍሪካ ቀንድ፣ ከቀይ ባሕር፣ ከዓባይ ሸለቆ፣ ከአረቢያ እና ከመካከለኛው ምሥራቅ አንጻር ከሀገሪቱ የተፈጥሮ አቀማመጥ እና ከየዘመኑ ዓለም አቀፍ ሁኔታ ጋር በቅርብ እና በጥብቅ የተያያዘ ጉዳይ እንደኾነ ነው የጻፉት።
ቀይ ባሕር እና የዓባይ ሸለቆ ለኢትዮጵያ ሥልጠኔ ምጥቀት እና ውድቀት አስተዋጽኦ አላቸው። ሁለቱን ታላላቅ ሀብቶች በተገቢው መንገድ ከተጠቀመች እድገቷ የላቀ፣ ሥልጣኔዋም የረቀቀ ይኾናል። ሁለቱን ሀብቶች በተገቢው መንገድ ካልተጠቀመች ግን አሉታዊ ተጽዕኖው የከፋ ነው።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ገናና መንግሥት ገንብታ እንደ እርሷ ሁሉ ገናና፣ ታዋቂ ከኾኑ የዓለም መንግሥታት እና ሕዝቦች ጋር የተገናኘችው በቀይ ባሕር እና በዓባይ ሸለቆ አማካኝነት ነው። የገናናነቷ ምክንያቶችም እነዚህ ናቸው።
እነዚህ ሀብቶች አያሌ በረከቶችን እንደሰጧት ሁሉ እነርሱን ብለው በሚመጡ ጠላቶችም ስትፈትን ኖራለች። ጠላቶች ተረባርበው በቀይ ባሕር ጠረፎች እና አካባቢው ላይ ተጽዕኖ ሲፈጥሩ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ እና እድገትም ፈተና ሲገጥመው በታሪክ ታይቷል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከባሕር በር እርቃ ምን አይነት ጫና እየደረሰባት እንደኾነ ማየትም ከታሪክ በላይ ሕያው ምስክር ነው።
የሀገሪቱ የቀይ ባሕር እና የዓባይ ሸለቆ ጂኦፖለቲካ እንደ ዘመኑ የዓለም ተጨባጭ ሁኔታ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የዕድገትም አስተዋጽኦ፤ የውድቀትም ተጽዕኖ ሲያደርግ ኖሯል። ለወደፊትም ሲያደርግ እንደሚኖር የታሪክ ልምድ እና የጂኦፖለቲካ ሕግ ያስተምረናል ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ።
ኢትዮጵያውያን ነገሥታትም ይሄን ጉዳይ ስለሚያውቁ ነው የባሕር በራቸውን እና የዓባይ ውኃ ተጠቀሚነታቸውን ለማረጋገጥ ሲታገሉ የኖሩት። የዚህ ዘመን ትውልድም ይህን በተገቢው መንገድ ስለተረዳ ነው የቀይ ባሕርን ጉዳይ የብሔራዊ ጥቅም እና የሕልውና ጉዳይ አድርጎት የተነሳው።
የታሪክ እና የባሕል ተመራማሪው ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ገናና ስም ያላት፤ ራሷን ነጻ አድርጋ የቆየች ገናና ሀገር ናት። ይህ ደግሞ ለአፍሪካ ኩራት እና አርዓያነት ነው፤ ተሰሚነቷ በአፍሪካ ብቻ ሳይኾን በዓለምም ገናና ነው ይላሉ።
ኢትዮጵያ በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ ሰላም አስከባሪዎች መካከል አንደኛዋ ናት። ተሰሚነቷ በቀጣናው እና በአፍሪካ ብቻ አይደለም በዓለምም ጭምር ነው እንጂ ይሏታል። ኢትዮጵያ አፍሪካን ወክላ ማማ ላይ የኖረች ሀገር ናት። ገናና ታሪኮቿ ተሰሚነቷን ከፍ አድርገውላታል ነው የሚሉት።
ይህ ገናና ታሪኳ እና ተሰሚነቷ እንዲቀጥል ደግሞ ዓባይን በተባባረ ክንድ ለጥቅም እንዳበቃችው ሁሉ የባሕር በርም ባለቤት መኾን አለባት ይላሉ። የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የነበረን ላግኝ እንጂ አዲስ ስጡኝ አይደለም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ለማሳከት ያልተቋረጠ እና የተቀናጀ የዲፕሎማሲ ሥራ ያስፈልጋል፤ ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማት የኢትዮጵያን እውነት፣ ከቀይ ባሕር ጋር ያላትን ግንኝነት፣ ታሪክ እና ጂኦፖለቲካ ጠቀሜታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስረዳት አለባቸው፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያንም በዚህ ጉዳይ ላይ መረባረብ አለባቸው ነው የሚሉት።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማረጋገጥ አስቀድሞ የውስጥ ሰላምን ለማረጋገጥ እና አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል። አንድነት ሲጠናከር በቀጣናው እና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰቡ ዘንድ የሚኖር ተሰሚነት ከፍ እንደሚልም አስገንዝበዋል።
“የአፍሪካ ምልክት እና የጥቁሮች አብነት የኾነችው ኢትዮጵያ” ገናናነቷ እንዲቀጥል አንድነት፣ ኅብረት እና ሰላም ከልጆቿ ይጠበቃል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
