በሰሜን ሸዋ ዞን 22 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡

269

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 08/2012 ዓ.ም (አብመድ) በሰሜን ሸዋ ዞን የኮሮናቫይረስ ከተገኘባቸው 22 ሰዎች መካከል 16 ሰዎች እየተፈለጉ መሆኑን መምሪያው አስታውቋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን ጤና መምሪያ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ አውላቸዉ ታደሰ ለአብመድ እንደተናገሩት በ79 ሰዎች ላይ ምርመራ ተደርጎ 22 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡

አስተባባሪ እንዳሉት ከ79 ተመርማሪዎች 36 አሽርካሪዎች ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል 16 የኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡ በቫይረሱ ከተያዙ ግለሰቦች መካከል አንደኛው በሞጃና ወደራ ወረዳ በአስከሬን ምርመራ መገኘቱም ታውቋል፡፡ ከሳምንት በፊት በእንሳሮ ወረዳ በቫይረሱ ተይዞ ሕይወቱ ካለፈ ሰው የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙና ከግለሰቡ ጋር የቀጥታ ንክኪ ከነበራቸዉ 45 ሰዎች መካል አራቱ በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡንም መምሪያው አስታውቋል፡፡

አንድ ግለሰብ ደግሞ ከጣርማበር ወረዳ ደብረሲና ከተማ ቫይረሱ ተገኝቶበታል፤ ግለሰቡ በአስተናጋጅነት ሥራ ላይ የተሰማራ እንደሆነም አስተባባሪው ለአብመድ ተናግረዋል፡፡

እንሳሮ ወረዳ ላይ የተገኘባቸዉ አራት ግለሰቦች ወደ ደብረ ብርሃን ለይቶ ሕክምና መስጫ እንዲመጡ እየተደረገ መሆኑም ታውቋል፡፡ ቫይረሱ ከተገኘባቸዉ 22 ሰዎች መካከል 16ቱ አሽከርካሪዎች የት እንዳሉ እንደማይታወቅና እየተፈለጉ እንደሚገኙ አስተባባው ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ ከግለሰቦቹ ጋር የቀጥታ ንክኪ ያላቸዉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የማግኘቱ ሥራ እንደተጀመረም ታውቋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኤልያስ ፈጠነ -ከደብረ ብርሃን

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleበአማራ ክልል ባለፉት 24 ሰዓታት 33 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው።
Next articleበኢትዮጵያ ተጨማሪ 176 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው፤ ሦስት ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል፡፡