
ባሕር ዳር: ጥቅምት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጣና በለስ የተቀናጀ የስኳር ልማት ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ያለውን የስኳር ምርት ችግር ለመቅረፍ በመንግሥት እና በሕዝብ ተስፋ ተጥሎበት፣ በሀገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የታመነበት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።
የፕሮጀክቱ ግንባታ በ2003 ዓ.ም ተጀምሮ በ18 ወራት ውስጥ በማጠናቀቅ ምርት እንዲያመርት በማሰብ ነበር ወደ ሥራ የተገባው። ፕሮጀክቱ 3 ፋብሪካዎችን በመገንባት ዘርፈ ብዙ የልማት ግቦችን በማስቀመጥ ከ75 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንዲያለማ ታስቦም ነበር የተጀመረው።
በታሰበው ልክ መጓዝ ባለመቻሉ በ2010 ዓ.ም የአሠራር ማሻሻያ ተደርጎለታል። በዚህ መሠረትም ከሦስቱ ፋብሪካዎች መካከል በአንዱ ፋብሪካ ላይ ትኩረት ተደርጎ ሲሠራ ቆይቷል። በዚህም አንደኛው ፋብሪካ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) በተገኙበት በ2013 ዓ.ም ተመርቆ የሙከራ ምርት ማምረት መጀመሩ ይታወሳል።
ሀገር የምትጠብቀውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለማስቻል በ2014 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 495/2014 ዓ.ም የስኳር ፋብሪካ ኾኖ ተቋቁሟል። ለጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ 110 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ካፒታል መፈቀዱም በደንቡ ተመላክቷል።
ነገር ግን ፕሮጀክቱ ባጋጠመው ውስብስብ ችግር ምክንያት እስከዛሬ ድረስ እውን ኾኖ በታሰበው ልክ ወደ ሥራ ባለመግባቱ እንዳሳዘናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
አበባው አዝመራው የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በአካባቢው እንዲሠራ በዕቅድ ተይዞ ወደ ተግባር ሲገባ ለአካባቢው ማኀበረሰብ ፈታኝ እንደነበር ያስታውሳሉ። ማኀበረሰቡ ከኖረበት ቀየ ለቅቆ ቤቱን አፍርሶ መሬቱን መልቀቁ ከባድ ነበር ይላሉ።
በወቅቱ በተደረገው መግባባትም የአርሶ አደሮች ኑሯቸው እንዲዘምን፣ የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ፣ የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርላቸው ተስፋ በማድረግ እና ከልማቱ ተጠቃሚ እንደሚኾኑ በማመን በርካታ አርሶ አደሮች መሬታቸውን ለፕሮጀክቱ መስጠታቸውን ያስረዳሉ።
ፕሮጀክቱ ሲጀምር ማኀበረሰቡን የመደገፍ፣ የሥራ ዕድል የመፍጠር፣ የማኀበራዊ ተቋማትን እና መሠረተ ልማቶችን የማሟላት ጅምሮች እንደነበሩት ጠቁመዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ ፕሮጀክቱ ማደግ ሲገባው በተቃራኒው እየተስተጓጎለ መምጣቱን ይገልጻሉ። በፕሮጀክቱ የተቀጠሩትን ሠራተኞችም በመቀነስ እስከመበተን እንደደረሰ አንስተዋል። በዚህ ምክንያትም የበርካታ ማኀበረሰብ ሕይወት ተመሠቃቅሏል፣ በፕሮጀክቱ የነበረውን ዕምነት አሳጥቷል፣ የቤተሰብ ሕይወት አደጋ ላይ ጥሏል ነው ያሉት።
የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቱ የገጠመውን ችግር ለይቶ በመፍታት በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ በማሥገባት በኩል መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራም ጠይቀዋል። የተበተኑት ሠራተኞችም እንዲመለሱ በማድረግ ሕይወታቸውን ሊታደጋቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ የሕዝብ ግንኙነት እና ተሳትፎ ኀላፊ አድገህ መኩሪያ ፋብሪካው በ2013 ዓ.ም ተመርቆ የሙከራ ምርት ማምረት ጀምሮ እንደነበር ገልጸዋል። አስከ 2015 ዓ. ም ድረስም በተወሰነ ደረጃ ስኳር ሲያመርት መቆየቱን ነው የተናገሩት። ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ግን ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ስኳር ማምረት ማቆሙን ገልጸዋል። በዚህ ምክንያትም በፋብሪካው በርካታ ሠራተኞች እንደተቀነሱም አረጋግጠዋል።
ለፋብሪካው ሥራ ማቆም ምክንያትም ሲያንቀሳቅሰው የነበረው የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር በመበላሸቱ የኤሌክትሪክ ኀይል በመቋረጡ መኾኑን አብራርተዋል። ከኀይል እጥረት ውጭ ፋብሪካውን ወደ ሥራ ለማስገባት ሌላ ችግር እንደሌለ ነው የገለጹት። የኃይል መቋረጥ ችግሩ ከተፈታ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ መግባት እንደሚችልም ነው ያረጋገጡት።
ፋብሪካው ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ በተጓዳኝ 7ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የአገዳ ልማት እየለማ ነው ብለዋል። ተጨማሪ 3ሺህ ሄክታር መሬት ላይ አገዳ ለማልማት እየተሠራ መኾኑን አብራርተዋል። የቀረው መሬትም ጦም እንዳያድር ታሳቢ ተደርጎ በ1ሺህ 544 ሄክታር መሬት ላይ በቆሎ፣ አኩሪ አተር እና ሩዝ እየተመረተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። በ119 ሄክታር መሬት ላይም የሙዝ፣ የማንጎ እና የብርቱካን ልማት እየለማ መኾኑንም አመላክተዋል።
ለአካባቢው ማኀበረሰብም ዘመናዊ የመኖ አቅርቦት፣ የሞላሰስ ምርት አቅርቦት፣ ዘመናዊ ግብርና ልማት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በመሠረተ ልማት ግንባታ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም አብራርተዋል።
አሁን ላይ እየተሠሩ ባሉት የልማት ሥራዎችም ለ510 ቋሚ እና ለ1ሺህ 500ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል። ፋብሪካው ሥራ በማቆሙ ምክንያት የተቀነሱ ሠራተኞችን ለመመለስም እየተሠራ ነው ብለዋል።
በቀጣይ ለሚሠሩት ሥራዎች ተጨማሪ 3ሺህ ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉ ጠቁመዋል። ሠራተኞች መጥተው የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ እንዲኾኑም ጥሪ አቅርበዋል።
ማኀበረሰቡ ተስፋ ሳይቆርጥ ባለቤት ኾኖ ክትትል እንዲያደርግም አሳስበዋል። የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎችም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል የሰሜን ምዕራብ ሪጅን የትራንስሚሽን እና ሰብስቴሽን ኦፕሬሽን እና ጥገና ኀላፊ ጌታቸው ተሻገር አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ትራንስፎርመር በመቃጠሉ ምክንያት ለፋብሪካው የሚያስፈልገው የኤሌክትሪክ ኀይል ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ መቆየቱን ተናግረዋል።
ለፋብሪካው ኀይል ለማቅረብ ከሰብስቴሽን እስከ ስኳር ፋብሪካው የሚያደርሱ ሰባት የሚኾኑ ኀይል ማስተላለፊያ ተሸካሚ ታወሮች በስርቆት ምክንያት መውደቃቸውን አንስተዋል። እነዚህን ታወሮች በቅርቡ የመጠገን ሥራ እንደሚሠራም ነው የተናገሩት።
በኢትዮጵያ ኢሌክትሪክ ኀይል የጀኔሬሽን ቢዝነስ ዩኒት የቴክኒክ ድጋፍ ኀላፊ ዮናስ ተስፋ ትራንስፎርመሩ ከውጭ ግዥ ተፈጽሞ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ በሱሉልታ ሰብስቴሽን ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በክልሉ ያለውን የጸጥታ ስጋት እና በመንገዱ አንዳንድ የድልድይ ብልሽቶች በመኖራቸው ትራንስፎርመሩን አጓጉዞ በቦታው ለማድረስ መቸገራቸውን አንስተዋል።
የጸጥታው ሁኔታ አስተማማኝ መኾኑ ከተረጋገጠ እና የድልድዮቹ ሁኔታ መፍትሔ ከተቀመጠ ትራንስፎርመሩ በማንኛውም ጊዜ አጓጉዞ ለመትከል ዝግጁ እንደኾኑም ጠቁመዋል።
ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ በቀን 12ሺህ ኩንታል ስኳር የማምረት አቅም አለው። በአጠቃላይ ለ23 ሺህ ዜጎችም የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል። ለልማቱም እስከ 24ሺህ ሄክታር መሬት እንደሚጠቀም ተመላክቷል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
