
ባሕር ዳር: ጥቅምት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ”የውጪ ባዕዳዎችን እና የውስጥ ባንዳዎችን ቅዠት በማምከን አንጸባራቂ ድሎችን እናስመዘግባለን” በሚል መሪ ሀሳብ ከከተማው የታክሲ እና ባጃጅ ትራንስፖርት ማኅበራት አመራሮች እና አባላት ጋር ውይይት አድርጓል።
የጸጥታ እና የሰዎች ደኅንነት ችግር፣ ሀገርን ከውጪ ጠላት ስለመጠበቅ፣ አገልግሎት አሰጣጥ እና ሌሎች ወቅታዊ ክልላዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ለውይይት ቀርበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የባጃጅ አሽከርካሪዎች የሥራ ሰዓት ገደብ ማሻሻያ እንዲደረግበትና የተሻለ አገልግሎት በመስጠት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ጠይቀዋል። ከአሽከርካሪዎች አልባሌ ጥቅም የሚፈልጉ አንዳንድ የጸጥታ አካላት መኖራቸውን ጠቅሰው እርማት እንዲወሰድም ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
ሕጋዊ አሽከርካሪዎች ሕገ ወጥ ተሽከርካሪዎችን በሚመለከቱበት ጊዜ ተከታትለው ለጸጥታ አካላት እንደሚጠቁሙም በመድረኩ ተነስቷል። ይሁን እንጅ በጥቆማው መሰረት ሕገወጦችን ተከታትሎ የመያዝ እና ርምጃ የመውሰድ ውስንነት ይስተዋላል ብለዋል ተወያዮቹ።
ለባጃጆች እንቅስቃሴ የተከለከሉ ቦታዎች መብዛት፣ የውስጥ መንገዶች ሁሉ በብረት አጥር ታጥረው መዘጋታቸው እንዲሁም የነዳጅ እና የመለዋወጫ እቃዎች ዋጋ መናር ችግሩን የከፋ አድርጎብናል፤ የትራንስፖርት ታሪፍ ግን መጨመር አልተፈቀደልንም ብለዋል። ስለኾነም ችግሮች እንዲፈቱ እና የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ አሽከርካሪዎች ጠይቀዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች ጉዳይ አማካሪ ብርሃኑ አበበ አሽከርካሪዎች ባነሷቸውን ጥያቄዎች ላይ ከተማ አሥተዳደሩ እንደሚወያይባቸው እና መፍትሔ እንደሚያበጅላቸው ገልጸዋል። አሽከርካሪዎችም ከሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ተቆጥበው፣ ሕገ ወጥነትን በመታገል ለከተማዋ ሰላም እንዲቆሙ አሳስበዋል፡፡
በመወያየት ችግሮች እየተፈቱ በመኾኑ ወጣቶች ለውይይት ዋጋ እንዲሰጡም አማካሪው ጠቁመዋል።
ሁሉም የየራሱን ችግር አይቶ በማረም ቀሪዎቹን ችግሮች በጋራ ተመካክረን እንፍታ፤ ለውጪ ጠላቶቻችን በር እንዳንከፍትም መጠንቀቅ አለብን ነው ያሉት።
የታክሲና ባጃጅ አሽከርካሪዎች ለከተማዋ ሰላም ተቆርቋሪ ኾነው መሥራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ የመንገድ ትራፊክ ዋና ክፍል ኀላፊ ኮማንደር አብርሃም ልየው አንዳንድ የባጃጅ አሽከርካሪዎች የሰላም ችግር እና ወንጀል እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል። ኅብረተሰቡም በባጃጅ ላይ ስጋቱ ከፍተኛ መኾኑንም አንስተዋል።
አሁን ላይ ሰላሙ እየተሻሻለ መኾኑን ጠቅሰው ችግሮች በአስተማማኝ ደረጃ ሲቀረፉ የባጃጅ እገዳው እንደሚነሳም አመላክተዋል።
የተሽከርካሪ እጥረት ሳይኖር ትርፍ መጫን እየተለመደ ነው ያሉት ኮማንደር አብርሃም ሕዝቡም እየተማረረ ስለኾነ የሕግ ማስከበርን ተገቢነት ገልጸዋል። የግል ችግር ያለባቸውን ተቆጣጣሪዎች ግን እየተከታተልን እናስተካክላለን ነው ያሉት።
ኮማንደር አብርሃም አሽከርካሪዎች ሕግን አክብረው በመሥራት እና ለሕገ ወጥ ትራፊኮች ባለመተባበር ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል ።
ከአሽከርካሪዎች አልባሌ ጥቅም የሚፈልግ የጸጥታ ኀይል ካለ በሚደርሰን መረጃ መሠረት እናርማለን ሲሉም ተናግረዋል።
በጸጥታ ተቋማት አካባቢ የተከለከሉ መንገዶች ተነስተዋል፤ በብረት ስለታጠሩ ሰፈሮችም ከማኅበረሰቡ እና ከሚመለከተው አካል ጋር እንመካከርበታለን ነው ያሉት። ወንጀለኞች ተደብቀው ለመንቀሳቀስ የተሸፈነ ባጃጅን ስለሚጠቀሙ ሽፋኑ መነሳቱን ጠቅሰው ሁኔታዎች እየታዩ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ ገልጸዋል።
የቁጥጥርም ኾነ የክልከላ ሥራ በመሠራቱ በባጃጅ ወንጀል መፈጸም መቀነሱን ያነሱት ኮማንደር አብርሃም ዘላቂው መፍትሔ ግን ሕግ እና ሥርዓትን አክብሮ ለሰላም በጋራ መሥራት መኾኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
