የማኅበረሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከል ተግባርን ማጠናከር ይገባል።

1
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላምና የጸጥታ ቢሮ የማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ሥራዎች ላይ ምክክር አድርጓል፡፡
የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደጀኔ ልመንህ የማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ባለቤት እንዲኾን የሚያደርግ ተግባር መኾኑን ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይም ከተፈጠረው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በአማራ ክልል የማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከልን በትክክል ተግባራዊ ለማድረግ ውስንነት መኖሩን አንስተዋል፡፡
ቀደም ሲል የማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀሎች ላይ ኅብረተሰቡ በራሱ ተነሳሽነት ሲሠራ እንደነበር አስታውሰዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን እየቀነሰ መጥቶ አሁን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል፡፡ አሁን ላይ ኅብረተሰቡን የጸጥታው ባለቤት በማድረግ መልሶ ለማንሠራራት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ስለማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ከጸጥታ መዋቅሩ ይጠበቃል ብለዋል።
ማኅበረሰቡ ደግሞ ተደራጅቶ እና ንቁ ኾኖ አካባቢው ላይ ወንጀል እንዳይፈጸም እና ከተፈጸመም ወንጀለኛን ለሕግ የመጠቆም እና የማቅረብ ሥራ ላይ እንዲተባበር ጠይቀዋል፡፡
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዋና መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ያሬድ አበበ ማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት በአማራ ክልል ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡ አጠቃላይ ሰላምና ጸጥታን ከማረጋገጥ ባለፈ ወንጀልን እና የወንጀል ስጋትን ለመቀነስ ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋልም ነው ያሉት፡፡ የተሠራው ሥራ ከወንጀል ነጻ የኾነ ቀበሌ እስከመፍጠር የደረሰ ብዙ ውጤት የተገኘበት መኾኑንም አንስተዋል፡፡
ማንኛውም ነባራዊ ሁኔታ ማኅበረሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከል ተግባርን ሊገድብ አይችልም፤ ኅብረተሰቡ ከራሱ ወጥተው በራሱ ላይ ወንጀል የሚፈጽሙበትን አካላት ተው ሊል እና ሊከላከል ይገባል ብለዋል፡፡
ኅብረተሰቡ የጸጥታ መዋቅሩን እንዲተባበር እና ውጤታማ ሥራ እንዲሠራም ጠይቀዋል፡፡ ኅብረተሰቡ ለራሱ ችግሮች ራሱ መፍትሔ እንዲኾንም አስገንዝበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ባሕር ዳር ከተማ በተሻለ ደረጃ የወንጀል መከላከል ተግባራትን ሢሠራበት መቆየቱን ገልጸዋል።
ከዓመታት በኋላ በነበሩ ሀገራዊ ችግሮች ምክንያት ግን የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ሥራዎች የተቀዛቀዙ መምጣታቸውን አንስተዋል።
በባሕር ዳር ከተማ ያሉ በርካታ የማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ማዕከሎች ወደ ነባር ተግባራቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል። ሕዝብን ያላሳተፈ የወንጀል መከላከል ሥራ ውጤታማ አያደርግም ያሉት አዛዡ አሁን ላይ በባሕር ዳር ከተማ ሕዝብን ያሳተፈ ሥራ እየተሠራ በመኾኑ ከቆዩ ሁኔታዎች አንጻር ለውጦች እየታዩ ነው ብለዋል፡፡ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ እያደገ መምጣቱ ውጤት እንዲመጣ ካደረጉ ጉዳዮች አንዱ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡
ባሕር ዳርን ጎብኝዎች እንደፈለጉ መጥተው የሚጎበኟት፣ የልማት ሥራዎች በተገቢው ሁኔታ የሚፈጸሙባት ሰላማዊ ከተማ ለማድረግ እንሠራለንም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleሰሞነኛው ጉንፋን መሰል ሕመም ምንድን ነው ?
Next articleየታክሲና ባጃጅ አሽከርካሪዎች ለከተማቸው ሰላም ተቆርቋሪ ኾነው መሥራት አለባቸው።