ሰሞነኛው ጉንፋን መሰል ሕመም ምንድን ነው ?

1
ባሕር ዳር: ጥቅምት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ መሠረት ባሕሩ የባሕርዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው። ከሰሞኑ ጉንፋን መሰል አዲስ ሕመም በልጆቻቸው ላይ በመከሰቱ ለሕክምና ወጭ፣ እንግልት እና ጭንቀት እንደዳረረጋቸው ገልጸዋል።
ልጆቻቸው መጀመሪያ ላይ ዓይናቸው አካባቢ የማሳሸት እና የማንባት ምልክት እንደታየባቸው፤ በአፍንጫቸውም ፈሳሽ እንደሚበዛ ተናግረዋል።
ጉንፋን ሊኾን እንደሚችል በመገመትም ሁሉንም አይነት የቤት ውስጥ ሕክምና ቢያደርጉም ልጆቻቸው እንዳልዳኑላቸው ነግረውናል።.ትኩስ ነገሮችን በመስጠት፣ በፍል ውኃ በማጠን እና ሞቃታማ ልብሶችን በማልበስ ጉንፋኑ በቶሎ እንዲድን ጥረት ቢያደርጉም እንዳልተሳካላቸው ጠቁመዋል።
ጉንፋን መሰሉ ሕመም ጠንከር ያለ እና ያልተለመደ ስሜት ያለው፣ የልጆቹን ሕመም የመቋቋም አቅም ያዳከመ፣ ከትምህርት ገበታቸውም የሚያስቀር በመኾኑ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ ግድ እንደኾነባቸውም ተናግረዋል።
ለመኾኑ ይህ በሽታ ምንድን ነው?
በጉዳዩ ላይ አሚኮ ያነጋገራቸው በወልድያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር ሀብታሙ መሰለ የክረምት ወራት ማብቃቱን ተከትሎ መስከረምን ጨምሮ በጥቅምት እና ኅዳር ወራት እንደዚህ አይነት ጉንፋን መሰል ሕመም የሚጠበቅ መኾኑን ተናገረዋል፡፡
ይህ ጉንፋን መሰል አደገኛ ወረርሽኝ የተለየ እና አዲስ የመጣ በሽታ ሳይኾን ያው የተለመደው የመተንፈሻ የአካል ክፍልን የሚያጠቃ እና የአየር መተላለፊያ ቧንቧዎችን የሚይዝ ጉንፋን ነው ብለዋል።
በተለምዶ “ሕዳር እስኪታጠን” እንደሚባለው ጉንፋኑን ሚያመጣው ቫይረስ የቅዝቃዜ ወራትን መውጫ ይዞ ለመራባት ምቹ ሁኔታን ስለሚያገኝ ሕመሙም በስፋት ይሰራጫል ነው ያሉት።
ይህ ጉንፋን ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው በትንፋሽ እና በንክኪ እንደኾነም ገልጸዋል። ሕመሙ ከአንድ ሳምንት በላይም ሊቆይ ይችላል ብለዋል።
የሰሞኑን ጉንፋን ለየት የሚያደርገው ሕጻናትን እና በዕድሜ ገፋ ያሉ ሰዎችን በስፋት ከማጥቃቱ በተጨማሪ ጠንከር ያለ የራስ ምታት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ከፍተኛ ትኩሳት፣ የመገጣጠሚያ ሕመም እና ቁርጥማት ያስከትላል ነው ያሉት።
በተለይ ደግሞ ሕጻናት ላይ ከፍተኛ የኾነ የምግብ ፍላጎት ማጣት እና የማጣጣም ስሜት መቀነስን ያስከትላል ብለዋል።
ይህንን ጉንፋን መሰል በሽታ ለመከላከል የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ መጠቀም፣ ጉንፋኑ ከያዘው ሰው ጋር ንክኪዎችን መቀነስ፣ ሰዎች በብዛት በሚገኙበት ቦታ ላይ መስኮቶች እና በሮች ካሉ መከፋፈት፣ የግል እና የአካባቢን ንጽሕና መጠበቅ እንደሚገባ መክረዋል።
በበሽታው የተጠቁ ሰዎች በሚያስነጥሱበት እና በሚስሉበት ወቅት አፍ እና አፍንጫን በአግባቡ መሸፈን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የተመጣጠነ ምግብ እና ትኩስ ነገሮችን ደጋግሞ መውሰድ፣ ንጽሕናን መጠበቅ እና በቂ እረፍት ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ይህ ጉንፋን መሰል በሽታ አሁንም ቢኾን እስከዚህ ጊዜ ይቆያል ብሎ ማስቀመጥ ስለማይቻል ሰዎች እንዲህ አይነት ሕመም ሲያጋጥማቸው ቤት ውስጥ ባለ ነገር እራሳቸውን መንከባከብ እና የሕመሙ ስሜት ጠንከር ካለ ደግሞ በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ አስፈላጊውን የሕክምና ምክር እና ዕርዳታ ማግኘት እንደሚችሉ አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ ሰመሀል ፍስሀ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማነቃቃት በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል።
Next articleየማኅበረሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከል ተግባርን ማጠናከር ይገባል።