
ባሕር ዳር: ጥቅምት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር” የውጭ ባዳዎች እና የውስጥ ባንዳዎችን ቅዠት በማምከን አንጸባራቂ ድሎችን እናስመዘግባለን” በሚል መሪ መልዕክት ከታክሲ እና የባጃጅ ማኅበራት መሪዎች እና አባላት ጋር ውይይት አድርጓል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ስንታየሁ ዘለቀ የውይይቱ ዓላማ በሰላም ሠርቶ እና ተንቀሳቅሶ ሕይዎትን ለመምራት እና እንቅፋቶችን በጋራ ለመከላከል መኾኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ጊዜያት ለጸጥታ መደፍረስ ምክንያቶች ምን እንደነበሩ በማየት እና በቀጣይ ተግዳሮቶች ላይም መምከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ከተማን ጸጥታ ለማረጋገጥ የከተማዋ ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ሀገራችን በጥንተ ጠላት ባዕዳን እና በባንዳዎች እየተፈተነች ነው ያሉት ኀላፊው አሁን ለገባንበት የግጭት አዙሪትም መነሻ ናቸው ብለዋል። ለውጭ ኃይሎች መሣሪያ የሚኾኑ እንዳሉም ገልጸዋል። ሁሉም ሀሳቡን እና ራሱን መመርመር አለበት ነው ያሉት።
የትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ አለመከፈት፣ ነጋዴዎች እንደልብ አለመንቀሳቀሳቸው የሰላሙ ችግር መገለጫ መኾናቸው ተገልጿል።
ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች እና የዲፕሎማሲ ሥራዎች ስኬቶች መኖራቸውም በመድረኩ ተመላክቷል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
